የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመሰራረትና የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች
ጥቅምት 03, 2008

በይርጋ አበበ

"ለዚህ ስፖርት እድገት የለፉትን በተለይም ይድነቃቸው ተሰማን እናመሰግናለን" ቀ.ኃ.ሥ

የቁም ህልመኛው ፋሽስቱ ቤኒቶ ሞሶሎኒ አገሩ ጣሊያን አድዋ ላይ የደረሰባትን የጦር ሜዳ ሽንፈት ክሽፈትም ሊባል ይችላል ከ40 ዓመታት ትዕግስት በኋላ በድጋሚ ኢትዮጵያን ለመውረር ያደረገው ጥረት በአገር ወዳድ ዱርቤቴዎች ማለትም ፋኖዎች ብርታትና እልህ አስጨራሽ ትግል ፋሽስት ከእናት አገር ኢትዮጵያ በተባረረበት የመጀመሪያ ዓመት ላይ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ጉልህ ስፍራ ይዞ የሚገኝ ታሪክ ተሰራ። በወቅቱ የአገሪቱ ንጉሠ ነገሥት በነበሩት አጼ ኃይለሥላሴ በጎ ፈቃደኝነት እና በአንዳንድ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን የእለት ተለት ድካም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተቋቋመ። ቀደም ሲል እንደገለጽነው ፌዴሬሽኑ የተቋቋመው ከጣሊያን ወረራ አንድ ዓመት በኋላ ሲሆን ጊዜውም እንደ ኢትዮጵያ የዘመን አሰላል 1936 ዓ.ም ነው።

ከ1936 ዓ.ም ጀምሮ እስካለንበት ዘመን ድረስ ያሉትን ዓመታት ብናሰላቸው 72 ዓመታት ይሆናሉ። ይህ ማለትም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከተቋቋመ 72 ዓመታትን እንደ ውሃ ፉት ያለ መሆኑን ነው። በእነዚህ 72 ዓመታት ፌዴሬሽኑ ምን ሰራ ምን አሳካ ወዘተ ጂኒጃንካ የሚሉትን የሪፖርት ዘገባዎች ለጊዜው ወደ ጎን ትተን ፌዴሬሽኑ በተመሰረተበት የመጀመሪያዎቹ 25 ዓመታት የተጓዛቸውን መንገዶች በመቃኘት ለአንባቢያን ማድረሱን መርጠናል።

በዚህ ሀሳብ ዙሪያ በየሳምነቱ በዚህ ቀን ዘገባዎችን የምናቀርብ መሆኑን እየገለጽን መረጃውን ያገኘነውም ፌዴሬሽኑ 25ኛ የብር እዮቤልዮ በዓሉን ባከበረበት ወቅት ያሳተመው ልዩ እትም መጽሔት መሆኑን እንድታውቁትም እንሻለን። ከፌዴሬሽኑ ልዩ ዕትም መጽሔት ላይ ያገኘናቸውን ሃሳቦች ሳንበርዝና ሳንደልዝ ከእነ ሙሉ ግርማ መጎሳቸውና ወዘናቸው ልናቀርባቸውም ወድደናል። በዚህ ዘገባ የኢትዮፉትቦል ዶትኮም ዘጋቢ ድርሻው አያያዥ ሀሳቦችን እንደ ጨው በትንሹ “ብትን ብትን” እያደረገ ማለፍ ብቻ መሆኑንም ከወዲሁ ይገልጻል። በዚህም መሰረት የመጽሔቱን ይዘትና ሀሳቦች ወደ መተረኩ እንሄዳለን። 

ማስታወሻ በፌዴሬሽኑ ልዩ ዕትም መጽሄት ላይ አንዳንድ ቃላት በአማርኛ ቢጻፉም በእንግሊዝኛው ትርጉማቸው በመሆኑ እኛ ወደ አማርኛ ቀይረን ተጠቅመንበታል። የዘመን ቀመሮቹም ሙሉ በሙሉ በሀበሽኛው ነው። ል.ዕ.መ ብለን የምንገልጻቸው ምህጻረ ቃላት ልዩ ዕትም መጽሔት የሚል የተብራራ ሀሳብ ይሰጣቸው። መልካም ጊዜ!!

የፌዴሬሽኑ የበላይ ጠባቂ ንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለሥላሴ ስለ ፌዴሬሽኑ

የኢትዮጵያ ፡ እግር ፡ ኳስ ፡ ፌዴሬሽን ፡ 25ኛውን ፡ ዓመት ፡ ሲያከብር ፡ በማየታችን ፡ በጣም ፡ ተደስተናል።  የዛሬ ፡ 25ዓመት ፡ ድርጅቱ ፡ ገና ፡ ለመቋቋም ፡ በሚራመድበት ፡ ጊዜ ፡ ከዚያም ፡ በጥርጊያ ፡ ሜዳ ፡ ላይ ፡ ጃንሜዳ ፡ ከጅቡቲ ፡ ቡድን ፡ ጋር ፡ ሲጋጠም ፡ በድንኳን ፡ ውስጥ ፡ ተቀምጠን ፡ የተመለከትንበትን ፡ ጊዜ ፡ እናስታውሳለን።

ይህ ፡ ስፖርት ፡ በኢትዮጵያ ፡ እንዲስፋፋ ፡ ያደረግነው ፡ ጥረት ፡ እና ፡ እርዳታ ፡ ዛሬ ፡ በአዲስ ፡ አበባ ፡ በአስመራ ፡ እና ፡ በድሬዳዋ ፡ እንዲሁም ፡ በልዩ ፡ ልዩ ፡ ጠቅላይ ፡ ግዛቶች ፡ በተሰሩት ፡ ስታዲየሞችና ፡ በውድድሩ ፡ ሀይል ፡ ድምቀት ፡ በማያቋርጠው ፡ ዓለም ፡ አቀፍ ፡ ግንኙነትና ፡ በየሳምንቱ ፡  ጊዜውን ፡ ስፖርት ፡ በመመልከት ፡ በሚያሳልፈውና ፡ ወደስታዲየም ፡ በሚጎርፈው ፡ ህዝብ ፡ ብዛት ፡ ፍሬ ፡ ያገኘ ፡ መሆኑን ፡ ተገንዝበናል።

የእኛን ፡ ምክር ፡ እና ፡ እርዳታ ፡ በመልካም ፡ ዘዴ ፡ ላይ ፡ በማዋል ፡ 25ዓመት ፡ ሙሉ ፡ በመከታተል ፡ ፌዴሬሽኑን ፡ የጠቅላይ ፡ ግዛት ፡ መመሪያዎችንና ፡ ክለቦችን ፡ በጉልበት ፡ በእውቀት ፡ በገንዘብ ፡ አገልግሎታቸውን ፡ የሰጡትን ፡ አባሎች ፡ ስናመሰግን ፡ ከጥንት ፡ ጀምሮ ፡ ለዚህ ፡ ስፖርት ፡ መመስረትና ፡ መስፋፋት ፡ ምክንያት ፡ የሆኑትን ፡ ሰውነታቸውንና ፡ ጊዜያቸውን ፡ ለዚህ ፡ ስፖርት ፡ አገልግሎት ፡ ያዋሉትን ፡ በተለይም ፡ ይድነቃቸው ፡ ተሰማን ፡ ልናመሰግን ፡ እንወዳለን። ል.ዕ.መ ገጽ 3!!

ከላይ የተቀመጠውን ሀሳብ የተናገሩት ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ነበሩ። በፌዴሬሽኑ 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ። ከቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ንግግር ለመረዳት እነደተቻለው ፌዴሬሽኑ ከመቋቋሙ በፊት አገሪቱ ውስጥ ስታዲየም አልነበረም። ስታዲየም አልነበረም ማለት ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ እግር ኳስ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ስፖርቶችም በፕሮፌሽናልነት ደረጃ ውድድር አይካሄድባቸውም ነበር ማለት ነው።

ሌላው ከንጉሰ ነገሥቱ ንግግር የሚገኘው ነጥብ ብሔራዊ ቡድናችን የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ጨዋታ ያደረገበትን ሜዳ እና የተጋጣሚውን ቡድን ማንነት ነው። ጃንሆይ ሜዳ ወይም በተለምዶ ጃንሜዳ ተብሎ በሚጠራው ሜዳ ላይ የተካሄደ ጨዋታ ሲሆን ጨዋታውን ያስጀመሩትም ንጉሰ ነገሥት አጼ ኃይለሥላሴ ነበሩ።

ከአጼ ኃይለሥላሴ ንግግር የተገኘው ሶስተኛውና ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ሀሳብ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምስረታ ገንዘባቸውን ጊዜያቸውን ሰውነታቸውን ማለትም ማንነታቸውን ሳይቀር እና እውቀታቸውን ሙሉ ያስተዋጹት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ መሆናቸውን ነው። የኢትዮጵያ ስፖርት አባት የሚል ስያሜ የተሰጣቸው አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ያበረከቱት አስተዋጽኦ እና ድካም ፌዴሬሽኑ አሁን ላለበት ደረጃ የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጣቸውን እናያለን።

የመጀመሪያው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ1936 ዓ.ም ቢቋቋምም የፌዴሬሽኑ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ግን የተመረጡት በ1941 ዓ.ም እንደነበረ ልዩ ዕትም መጽሔቱ ያስረዳል። የፌዴሬሽኑ የመጀመሪያው ሊቀመንበርም ሌፍቴናንት ጄኔራል ከበደ ገብሬ ይባላሉ። ጄኔራል ከበደ ገብሬ በፌዴሬሽኑ 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ ለተዘጋጀው ልዩ ዕትም መጽሔት አጠር ያለ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን እኛ ደግሞ ለአንባቢያን በሚመች መልኩ ቀንበብ አድርገን እናቀርበዋለን።

ጄኔራሉ የፌዴሬሽኑ ሊቀመንበር ሆነው የሰሩባቸውን ዓመታት በመጥቀስ መናገር ይጀምሩና እንዲህ ይላሉ። 

“በዚያን ፡ ጊዜ ፡ ይህ ፡ የእግር ፡ ኳስ ፡ ፌዴሬሽን ፡ ገና ፡ በመቋቋም ፡ ደረጃ ፡ ላይ ፡ ነበር። ፡ ስፖርት ፡ በተለይም ፡ የእግር ፡ ኳስ ፡ ጨዋታ ፡ በኢትዮጵያ ፡ ከተጀመረ ፡ ቅርብ ፡ አልነበረም ፡ ቢባልም ፡ ፌዴሬሽኑ ፡ ግን ፡ የመጀመሪያው ፡ መሆኑ ፡ ይታወሳል” ፡ ብለዋል።  ጄኔራል ፡ ከበደ ፡ ገብሬ ፡ ከዚህ ፡ በተጨማሪም ፡ “የፌዴሬሽኑ ፡ ዋና ፡ ስራ ፡ አስኪያጅ ፡ የነበሩት ፡ አቶ ፡ ይድነቃቸው ፡ ተሰማ ፡ በጠቅላላይ ፡ የስፖርት ፡ ኮንፌዴሬሽን ፡ በተለይም ፡ የእግር ፡ ኳስ ፡ ፌዴሬሽን ፡ ዛሬ ፡ እሚገኝበት ፡ ደረጃ ፡ መድረስ ፡ የቻለው ፡ በአቶ ፡ ይድነቃቸው ፡ ተሰማ ፡ ለተቋሙ ፡ ነብስ ፡ በመሆን ፡ ተንቀሳቅሶ ፡ ነው ፡ ብል ፡ ቃል ፡ አጋኖ ፡ ሆኖ ፡ የሚገመት ፡ አይመስለኝም።” ሲሉ ገልጸው ነበር።

የአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ቃል

አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ሆነ በእግር ኳሱ እድገት ላይ ያስተዋጹት ውለታ በተደጋጋሚ ጊዜ ተነግሯል። ያም ሆኖ አይበቃም የተነገረውም ሲያንሳቸው ነው። በተለምዶ በአገራችን አንድ አባባል አለ “የተውሶ በሬ ወደ ቤቱ ይስባል” የሚል። እኛ ኢትዮጵያዊያን ግን ወደ ቤታችን ሳይሆን ወደ ውጭ መሳብም ሆነ መሳብ’ ይቀለናልም ይቀናናልም። በዚህ ጉዳይ ማለትም በአቶ ይድነቃቸው ታሪክና የስራ ጥረት በተመለከተ ወደፊት የምንመለስ ይሆናል። ዛሬ ግን በፌዴሬሽኑ 25ኛ ዓመት በዓል ሲከበር የክብር ዋና ጸሀፊ የነበሩ ሲሆን ስለፌዴሬሽኑም ይህን ብለው ነበር።
Yidnekachew Tessema

የኢትዮጵያ ፡ እግር ፡ ኳስ ፡ ፌዴሬሽን ፡ የተመሠረተበትን ፡ 25ኛ ፡ ዓመት ፡ መነሾ ፡ በማድረግ ፡ ይህችን ፡ መጽሔት ፡ ለህዝብ ፡ ስናቀርብ ፡ ደስታ ፡ ይሰማናል። ፌዴሬሽናችን ፡ በያመቱ ፡ የስራና ፡ የሂሳብ ፡ ራፖሮች ፡ እንጂ ፡ የተጠናቀቀ ፡ ያመት ፡ ማስታወሻ ፡ ስላላሳተመ ፡ በዚህ ፡ መጽሔት ፡ ውስጥ ፡ የ25 ፡ ዓመት ፡ ማስታወሻ ፡ ተጠቃሎ ፡ እንዲገኝ ፡ አድርገናል” ፡  ሲሉ ስለመጽሔቱ ዝርዝር መረጃ ተናግረዋል።
 
የፊፋው ፕሬዚዳንት አቶ ስታንሌይ ሮውስ

ሚስተር ስታንሌይ ሮውስ በ1961 በእኛው የዘመን ስሌት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ስለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገትና አጠቃላይ ጉዞ ከዚህ በታች ያለውን ሀሳብ አቅርበው ነበር። መጽሔቱም የፊፋውን ፕሬዚዳንት መልዕክት በመጽሔቱ ልዩ እትም ላይ አስፍሮት የተገኘ ሲሆን ለዚህ ዘገባችን ተስማሚ ሆኖ ስላገኘነው እኛም ጽፈን አቅርበንላችኋል። የፕሬዚዳንቱን ሀሳብ በራሳቸው አፍ ለመጻፍም አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘነው እንግሊዝኛውን ተጠቅመናል።
Majesty Hailesselassie Meeting with FIFA President

On behalf of FIFA I am pleased to offer congratulations to the Ethiopian F.A on reaching its 25th anniversary. During that time the Association has been a loyal member of FIFA has made much progress in the development of the game has produced international players and referees and for years has been represented on FIFA and African Confederations by Mr. Yidnekachew Tessema.

The Association has enjoyed Royal Patronage, organized tournaments, referee courses and conferences and, it is hoped will continue to prosper in all its activities.

Stanley Rous President FIFA 1969 G.C

ውድ አንባቢያን በቀጣዮቹ ክፍሎች ደግሞ የሌሎችን የፌዴሬሽኑ የስራ ኃላፊዎች ቃል ይዘን የምንመለስ ሲሆን ይህንን ታሪክ መከታተል የምትችሉት በየሳምንቱ ዕለተ አርብ  መሆኑንም በድጋሚ እንገልጻለን።

ይቀጥላል!!

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!