የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሜዳው በኮንጎ አቻው 4ለ3 ተሸነፈ።
ህዳር 04, 2008

ፈለቀ ደምሴ

ዛሬ ከኮንጎ አቻው ጋር ለ2018ቱ ለሩሲያው የአለም ዋንጫ ለማለፍ የማጣሪያ ጨዋታውን አዲስ አበባ ላይ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 4ለ3 በሆነ ውጤት ተሸንፏል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጌታነህ ከበደ በ42ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው ጎል መምራት ቢችልም ኮንጎዎች ምላሽ ለመስጠት ከሁለት ደቂቃ ተኩል በላይ አልወሰደባቸውም። በ44ኛው ደቂቃ ላይ ያገኙትን ቅጣት ምት በ13ት ቁጥሩ ቢፎማ ኬ.ተዬሪ አማካኝነት ወደ ጎል በመቀየር የመጀመሪያው 45 ደቂቃ ጨዋታው በአቻ  1ለ1 ውጤት እንዲጠናቀቅ ማስገደድ ችለዋል። 

Congo Equalizer


ከረፍት መልስ ከመጀመሪያውም ቢሆን የመሃል ሜዳውን ተቆጣጥረውት የዋሉት ኮንጎዎች የጨዋታ የበላይነት በመያዝ የዋልያዎቹን የተከላካይ ክፍል በማስጨነቅ በ61ኛው በ74ተኛውና በ80ናኛው ደቂቃዎች ላይ ሶስት ጎሎችን አከታትለው በማስቆጠር  ጨዋታውን 4ለ1 መምራት ቻሉ። አሰልጣኝ ዮሃንስ ቡድናቸው ሶስት ለአንድ እስኪመራ ድረስ የተጫዋች ለውጥ አለማድረጋቸው ቡድናቸውን ሲጎዳው ታይቷል። በተለይ 10 ቁጥሩ በረከት ይሳቅ ለቡድኑ ምንም ሲያገለግል ባልታየበት በዛሬው ጨዋታ እስከ ሰባ አምስተኛው  ደቂቃ በሜዳ ላይ መቆየቱ አግባብነት አልነበረውም። ዘግይተውም ቢሆን ኤልያስ ማሞና  በሃይሉ ግርማ ጨዋታው አስራ አምስት ደቂቃ ሲቀረው ተቀይረው ወደ ሜዳ በመግባታቸው ለቡድኑ የመነቃቃትን ስሜትን መፍጠር ችለዋል።  በተጫዋቾቹ ለውጥ የተነቃቁት ዋልያዎቹ  በሰፊ ጎል ከመሸነፍ ቡድኑን ያዳኑትን 2ለት ጎሎች በ81ኛው ደቂቃ ላይ በዳዊት ፈቃዱ እንዲሁም በ90ኛው ደቂቃ ላይ በሽመልስ በቀለ አማካኝነት  ማስቆጠር ቢችሉም  ለጨዋታው የተመደበለት ሰአት በማለቁ ጨዋታው በኮንጎ ብሄራዊ ቡድን   የበላይነት 4ለ3 በሆነ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል። 

 በዛሬው ጨዋታ እንደታየው የኮንጎ ብሄራዊ ቡድን ጠንካራ ቡድን ነው። በመሆኑም ለአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ከሜዳቸው ውጪ የሚያደርጉትን የመልስ ጨዋታ የበለጠ ፈታኝ እንደሚሆንባቸው ይጠበቃል። በተጫዋች ምርጫቸውና አሰላለፍ ላይ እንደዚህ ያለ ከባድ ጨዋታን ሊቋቋሙ የሚችሉ ተጫዋቾችን ማሰለፍ ይጠበቅባቸዋል በዚህ እረገድ በአጥቂ መስመር በቡሩንዲው ጨዋታ ተቀይሮ ገብቶ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የታዘብነው ምንይሉ ወንድሙን እንዲሁም በተከላካይ መስመር   ዋሊድ አታን በመልሱ ጨዋታ ቢያሰልፉ ልጆቹ ካላቸው የአካል  ብቃትና የኳስ ጥበብ ቡድኑን የተሻለ  ውጤት እንዲያስመዘግብ ሊረዱት ይችላሉ እንላለን።

በመልሱ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን  ወደቀጣዩ የማጣሪያ ጨዋታ ለማለፍ በሁለት ጎል ልዩነት ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ምንም እንኳን   ከሜዳ ውጪ  በሁለት ጎል ልዩነት እንደ ኮንጎ ያለ ጠንካራ ብሄራዊ ቡድንን  አሸንፎ ማለፍ ከባድ ቢመስልም የማይቻል ነገር ግን አይደለም። አሰልጣኝ ባሬቶ አዲስ አበባ ላይ በማሊ 2ለ0 ተሸንፈው ባማኮ ላይ  በ10 ተጫዋች ከ30 ደቂቃ በላይ እንዲጫወቱ በተገደዱበት ሁኔታ ተስፋ ሳይቆርጡ ጠንካራውን ማሊን በሜዳው 3ለ2 ማሸነፍ የቻሉበት የቅርብ ጊዜ ታሪክ ለቡድናችን ጥሩ እንደማነቃቂያ ምሳሌ ሊሆን ይችላል።

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ከጨዋታው በኋላ ስለጨዋታው ለጋዜጠኞች የሰጡት መግለጫ

አሰልጣኝ ዮሃንስ ከጨዋታው በኋላ ለጋዜጠኖች በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ስለጨዋታው የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል።
Yohannes Sahle Head Coach The Walya

 
"እነሱ ከሚጫወቱበት ፕሮፌሽናል ክለቦች፣ ካላቸው ብቃት አንጻር ስናይ በጨዋታ አልተናነስንም እነሱ አራት አገቡ እኛ ሶስት አገባን በጎል አልተናነስንም። ነገር ግን በብቃት ከኛ የተሻሉ ተጫዋቾች አሏቸው። ሲያጠቁ ያጠቃሉ ሲከላከሉም እንደዛው። ያገኙትን እድል በሚገባ ይጠቀማሉ እኛ አንዳንድ ጊዜ የምናገኛቸውን እድልሎች አንጠቀምም። በጨዋታው መሃል ላይ በልጠውናል። መሃል ላይ ያላቸው ልምድ ኳስ አደረጃጀታቸው ከኛ የተሻለ ነበር ብለዋል። "

ለቡድናቸው መመሪያና ምክር ወደሜዳ ጠርዝ እየገቡ ለምን እንዳልሰጡ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ። ጨዋታው የተጫዋቾች ነው የሚገባቸውን ምክርና መመሪያ እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስ ስንመካከር ቆይተናል። 90 ደቂቃ ቆሞ መጮህ ህጉም አይፈቅድም። አስፈላጊውን ምክር ፋሲልም አሊም በተገቢው ሰአት ከመቀመጫቸው እየተነሱ ሲሰጡ ነበር። እኔም በነፋሲል በኩል ሲያስፈልግ ተገቢውን መልእክት አስተላልፌያለሁ። በእረፍት ሰአት ብንሸነፍም እንሸነፍ ገፍታችሁ ጎል ለማግባት ተጫወቱ ብዬ መክሬያቸዋለሁ።  90 ደቂቃ ቆሞ የሜዳ ጠርዝ ላይ በመጮህ ግን አላምንበትም። ለምሳሌ 90 ደቂቃ ቆሜ የምጮህ ከሆነ ይሄ ሰው የቤት ሥራውን ሰርቶ አይመጣም ነበር ብለህ ልተወቅሰኝ ትችላለህ። ይሄ እንግዲህ እነደየ አሰልጣኙ አመለካከት ይለያያል እኔ እራሴን  ዮሃንስ ነው መሆን የምችለው። ነገር ግን ይሄን ስልህ ሃሳብህን  እንደ ሀሳብ እቀበለዋለሁ።

ለመልሱ ጨዋታ ምን እነደሚያስቡ ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ አንድ እድል ነው ያለን ማሸነፍ ብቻ  ስለዚህ መቶ በመቶ ለማሸነፍ እንሰራለን ለማሸነፍም ነው የምንጫወተው ብለዋል። 

አሰልጣኝ ክላውድ ሊ ሮይ ከጨዋታው በኋላ ስለጨዋታው ለጋዜጠኞች የሰጡት መግለጫ

በዜግነት  ፈረንሳዊ የሆኑት የኮንጎው አሰልጣኝ ክላውዲ ሊ ሮይ  ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ።
Congo Coach Coude Li Roy

በመጀመሪያ ዜግነታቸው ፈረንሳዊ እንደመሆኑ በትላንትናው ሌሊት በፓሪስ በደረሰው የአሸባሪዎች አደጋ ምክንያት ሌሊቱ ለሳቸው ከባድ እንደነበር አስታውሰው። በአደጋው ለሞቱት በዛሬው ጨዋታ መጀመሪያ ላይ የህሊና ጸሎት እንዲደረግላቸው ለፊፋ ባለስልጣናት ለዳኛው ለጨዋታው ኮሚሽነር ጨምሮ ከጨዋታው በፊት ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም የፊፋ መመሪያ አልደረሰንም በሚል የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት ባለመደረጉ እንዳዘኑ ገልጸዋል። እንደዚህ አይነት አደጋ በኢትዮጵያ አልጄሪ በናይጄሪ እንዲሁም በሌሎችም  የአፍሪካ ሃገራትም ጭምር   ከዚህ በፊት ተከስቶ ያውቃል። እንደዚህ አይነት አደጋ ሲደርስ በየትኛውም አለም ብራዚል አርጀንቲና   ተጎጂዎችን በማሰብ በስፖርት አደባባይ የህሊና ጸሎት ይደረጋል። መመሪያን መጠበቅ የሚያስፈልግ ጉዳይ አልነበረም በማለት ቅሬታቸውን ጨዋታውን በመሩት የፊፋ  ባለስልጣናት ላይ የተሰማቸውን ቅሬታ በመግለጥ ስለጨዋታው አስተያየታቸውን መስጠት ጀምረዋል።

ስለጨዋታው በሰጡት አስተያየት ጨዋታው ብዙ ጎል የተቆጠረበት ጥሩ ጨዋታ እንደነበረና  ቡድናቸው በማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወትን ስለሚጫወት ባለፉት ሁለት አመታታት ብዙ ጎል እያስቆጠረ ጨዋታዎችን የማሸነፍ ልምድ እንዳለው ሲገልጹ ጊኒቢሳኦ ላይ 4ት ናይጄሪ ላይ 3ት ጎሎችን ማስቆጠራቸውን በማስታወስ ነበር።

ቀጥለውም የፊት መስመር ተጫዋቻቸው 13ት ቁጥሩ ቴሪ ምንም እንኳን ጎበዝ ተጫዋቻቸው ቢሆንም በተደጋጋሚ በሰራው ጥፋት ተመልካቹን ማበሳጨቱ እንዳላስደሰታቸውና እሳቸው በታሪካቸው ተጫዋቾቻቸው ሆን ብለው ጥፋት እንዲሰሩ የማያበረታቱ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ስለ ተጋጣሚያቸው የኢትዮጵያ ቡድን ሲናገሩም ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ጀምሮ ትልቅ ግምት የሚሰጡት ቡድን እንደሆነ ተናግረው። በታሪክም ቢሆን ኢትዮጵያ ለኔ ትልቅ ቦታ አላት ደጋግሜ መምጣትን እፈልጋለሁ ኋይለሥላሴ እንደሁም ቦምበርሌን አስታውሳለሁ። 

በተለይ ደቡብ አፍሪካ ላይ ዋሊያዎቹ በሚያስደንቁ ደማቅ  ደጋፊዎቻቸው ታጅበው አሳይተውት የነበረው ምርጥ ጨዋታ የሚደነቅ ነው ሲሉ ተናግረዋል። አያይዘውም ሲናገሩ አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከዚህ ቀደም በማሊ አዲስ አበባ ላይ 2ለ0 ቢሸነፍም  ባማኮ ላይ 3ለ2 ማሸነፍ የቻለ ቡድን እንደሆነ እናስታውሳለን። በመሆኑም ማክሰኞ የምናደርገውን የመልሱን ጨዋታ በቀላሉ አናየውም በተከላካይ በኩል ዛሬ የሰራናቸውን ስህተቶች ለማረም እንሰራለን ብለዋል። 


የአዲስ አበባ ከፍተኛ አልቲትዩድ ላይ እንደመገኘቷ ቡድናቸው እንዴት እስከመጨረሻው ተጭኖ ለመጫወት ብርታቱን እንዳገኘ ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ። 

እግር ኳስ ጨዋታ ነው። ጨዋታ መሆኑን መቀበልና ማክበር ያስፈልጋል። መጫወት ይኖርብናል ። ጨዋታ መሆኑን ከረሳን ግን ሁሉንም ነገር እንረሳዋለን። የእኔ የኳስ አጨዋወት ፍልስፍና የቆየ ነው ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ኳስን በመጫወትና በማጥቃት ላይ የተመሰረተን አጨዋወት ነው የምከተለው ያው መከላከልም እንዳለ ሆኖ። በመሆኑም የአልቲቱድ ልዩነት አጨዋወታችንን አይቀይረውም በማለት መልሰዋል።

ሁለቱ ቡድኖች የፊታችን ማክሰኞ የመልስ ጨዋታቸውን ኮንጎ ላይ የሚያደርጉ ይሆናል።


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Gizegeta [830 days ago.]
 በጣም ያሳፍራል የኮቹ ስራ በገዛ ሜዳው በደጋፊው ፊት ሽንፈትን መከናነቡ ሲጀመር ለሽንፈቱ ተጠያቂው አሰልጣኙ ብቻ ነው:: ስንት መመረጥ የሚገባቸው ተጫዋቾች እያሉ እንደ አስራት መገርሳ ....አዲስ ህንፃ.... ምንተስኖት.... በሃይሉ አሰፋ.... ናቲ....ተስፋዬ ቆቦ.... ባዬ ገዛኸኝ ....አይነቶችን ሆን ብሎ የራሱን ክሬዲት ከፍ ለማድረግ የራሱን ብድን ሰራ ለመባል ዘለላቸው :: በጣም ያሳፍራል ብሔራዊ ቡድኑን ፓርላማ ይመስል በኮታ አድርጎታል :: ስንት ብሔራዊ ቡድኑን መጥቀም የሚችሉ ጀግኖች እያሉ በዚህ ሰውዬ ግትርነት ሳይመረጡ መቅረታቸው እጅግ በጣም ያሳዝናል ያሳፍራል !!! ኮች ሰውነት ቢሻው ይግደለን ! አረ መልሱልን ሰውነት ቢሻውን..... ጀግናውን !!!

Dani man [830 days ago.]
 ይሄ ቡድን ይሄ ስብስብ ነው ለአለም ዋንጫ የሚያልፈው ? አይደለም ለአለም ዋንጫ ለአፍሪካ ዋንጫ አያልፍም የዮሃንስ ስብስብ :: አረ እንደውም ለሴካፋም ዋንጫ ከምድቡ ማለፉን እጠራጠራለሁኝ:: ፌዴሬሽኑ በምን መስፈርት ነው ለብሔራዊ ቡድኑ ኮች የሚመርጠው ? እስከ 70 ደቂቃ ድረስ ስህተቶችን አይቶ ቅያሪ ማድረግ የማይችል ኮች ምኑን ኮች ሆነው! በዚህ ላይ ከጨዋታ በሃላ የሚሰጣቸው መግለጫዎች ያስቃሉ....." ኮንጎ ትልቅ ቡድን ነው ምናምን እነሱ ከሚጫወቱበት ፕሮፌሽናል ክለቦች፣ ካላቸው ብቃት አንጻር ስናይ በጨዋታ አልተናነስንም እነሱ አራት አገቡ እኛ ሶስት አገባን በጎል አልተናነስንም" ሃሃሃሃሃሃ አይዞህ ሁልጊዜ ከቡርንዲ.... ከሶማሊያ.... ከሲሸልስ .... ጋር ፊፋ ይደለድልሃል ግን ምን ዋጋ አለው እነሱም ይከብዱሃል :: ኮንጎን በገዛ ሜዳህና ደጋፊህ ፊት በአየሩ አድቫንቴጅ ተጠቅመህ ማሸነፍ ካልቻልክ ታዲያ እንዴት ሆኖ ነው ለአፍሪካ ዋንጫ የምታልፈው ?????????????? ቻንስ ላይ ምን ልትሆን ነው ?????????

Yoni Sanjawe [830 days ago.]
 የመልሱ ጨዋታ ላይ ስንት ጎል እንደሚያስተናግድ ለማየት ቸኩያለሁ ወይኔ እማማ ኢትዮጵያዬ ማንም እየተነሳ ኮች እየሆነ በሰውነት ቢሻው ጊዜ ተከብረሽ የነበርሽው ሃገር በዮሃንስ ጊዜ በሱማሊያ በሲሸልስ በቡርንዲ በኮንጎ ተቀለደብሽ !

felexsami [830 days ago.]
 ለሽንፈታችን ተጠያቂው አሰልጣኝ ተብዬው ዮሃንስና ዮሃንስ ብቻ ነው:: ምክንያቱም ብሔራዊ ቡድኑን የሚፈልጠው የሚቆርጠው እሱ ብቻውን ነው ያሻውን የሚጠራው ያሻውን የሚያባርረው .... ስንት መመረጥ የሚገባቸውን ልጆች ሃገራቸውን መጥቀም የሚችሉ ልጆችን ሆን ብሎ ዘሏቸዋል እድል ነፍጓቸዋል its shame.

Mali [830 days ago.]
 እነ አስራት:..... እነ ምንተስኖት:..... እነ ተስፋዬ ቆቦ:...... እነ ናቲ:..... እነ በሃይሉ ....እነ ምንያህል.... የትላንትናውን ኮንጎ ማቆም ያቅታቸዋል ? I dont think soooooo አረ ግፍ ነው እየተሰራ ያለው !

yilkal [830 days ago.]
 1.ሽንፈታችን ተጠያቂው አሰልጣኝ ዮሃንስ Bicha Sayihon Ethiopian foot ball federation 2. ይሄ ቡድን ይሄ ስብስብ ነው ለአለም ዋንጫ የሚያልፈው ? አይደለም ለአለም ዋንጫ ለአፍሪካ ዋንጫ አያልፍም የዮሃንስ ስብስብ(Correct) 3.በጣም ያሳፍራል ብሔራዊ ቡድኑን ፓርላማ ይመስል በኮታ አድርጎታል(Correct) 4, ስንት ብሔራዊ ቡድኑን መጥቀም የሚችሉ ጀግኖች እያሉ በዚህ ሰውዬ ግትርነት ሳይመረጡ መቅረታቸው እጅግ በጣም ያሳዝናል ያሳፍራል !!! ኮች ሰውነት ቢሻው ይግደለን ! አረ መልሱልን ሰውነት ቢሻውን..... ጀግናውን !!! Correct Gizegeta, Dani man. Yoni Sanjawe, felexsami thank you very much for your comment. Keep it up. the above mention critics are very important if EFF listen.

Melaku [830 days ago.]
 ትክክለኛ ፍትሃዊ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ምርጫ የተካሄደ ቢሆን ኖሮ ዮሃንስ ከእነ አስራት ሃይሌ ከእነ ስዩም ከበደ ከእነ ውበቱ አባተ ከእነ ገብረመድህን ሃይሌ ጋር ተወዳድሮ አሸናፊ ይሆናል ማለት ዘበት ነው:: በምን መስፈርት ፌዴሬሽኑ አሰልጣኝ አድርጎ እንደሾመው የስፖርት ተመልካቹ የዘወትር ጥያቄ ነው::

yilkal [830 days ago.]
 ኮችኮች ሰውነት ቢሻው ይግደለን ! አረ መልሱልን ሰውነት ቢሻውን..... ጀግናውን !!! Return Sewnet Bishaw !!!!

Dani man [829 days ago.]
 ሁልጊዜ የምትሰጠው ኮመንት ትዝብት ላይ ይጥልሃል:: ተሸንፈን 4 ጎሎች በሜዳችን አስተናግደን የማለፍ እድላችን ጠቦ ውጤቱ መጥፎ አይደለም ትላለህ ?! ቂል ነገር ነህ !!!

Dani man [829 days ago.]
 @ Tanoo ሁልጊዜ የምትሰጠው ኮመንት ትዝብት ላይ ይጥልሃል:: ተሸንፈን 4 ጎሎች በሜዳችን አስተናግደን የማለፍ እድላችን ጠቦ ውጤቱ መጥፎ አይደለም ትላለህ ?! ቂል ነገር ነህ !!!

tanoo [829 days ago.]
 The result is not bad.we should not exagurate the deafeat.we have to give the team support after all we jave to admire that they where able to score 3 goals. The game was not an easy one congo is a though team.

tanoo [829 days ago.]
 The result is not bad.we should not exagurate the deafeat.we have to give the team support after all we jave to admire that they where able to score 3 goals. The game was not an easy one congo is a though team.

Ashenafi Tesfaye [829 days ago.]
 እርማት/ ኤልያስ ማሞ ተቀይሮ አልገባም በጋቶች ብሩክ ቃልቦሬ ነው የገባው።

Ashenafi Kebede [829 days ago.]
 የቻን የምድብ ዕጣ ድልድልን ባየሁኝ ጊዜ ዮሃንስ አሳዘነኝ ሃሃሃሃሃ በዚህ ስብስቡ በእነ ካሜሮን አንጎላ ኮንጎ ሲቀለድበት ታየኝ ::

Dani man [829 days ago.]
  እኔም ታይቶኛል በካሜሮን በአንጎላ በኮንጎ ሲቀለድበት ዮሃንስ ሯዋንዳ ላይ lol መሃረቤን ያያችሁ አላየንም .... መሃረቤን ያያችሁ አላየንም .... መቼም እዚህ ስብስብ ላይ በረኛ ሆኖ የሚሄደው ተጫዋች ፈረደበት ታየኝ በኳሶቹ ሲደበደብ በኳሶቹ ሲያባብጥ ሃሃሃሃሃ

Samuel Bezabeh [829 days ago.]
 ይህንን ስብስብ ይዞ አሳፋሪ ውጤት ይዞ ከቻን እንደሚመለስ ምንም ጥርጥር የለውም ኧረ የፌዴሬሽኑ ሰዎች ዮሃንስን ምከሩት?! በግፍ ከብሔራዊ ቡድኑ የታለፉ ምርጥ ብቃት ላይ ያሉት ልጆች በአስቸኳይ ቡድኑን ይቀላቀሉ:: የአሁኑ የዮሃንስ ስብስብ አይደለም ለአለም ዋንጫ አይደለም ለአፍሪካ ዋንጫ አይደለም ለቻን ለሴካፋ የሚመጥኑ አይደሉም::

Leul Mekonen [829 days ago.]
 ከኮንጎ ጋር ያየነው ብድን ምንም ተስፋ ያለው አይመስልም አሰልጣኙ ለምን ልምድ ያላቸውን ተጫዋች ከአዲሶቹ ጋር ቀላቅሎ መጠቀም እንዳልፈለገ ግርም ነው የሚለኝ:: እስቲ ጋዜጠኞች ጠይቁልን ለምንድነው የኮች ሰውነት ቡድን ውስጥ ሆነው የነበሩትን ጥሩ አቋም ላይ የሚገኙትን ልጆች ለምንድነው ጥሪ የማያደርግላቸው ? እኛም እኮ ተመልካቾች ማን ጥሩ አቋም ላይ እንዳለ ማን ደግሞ አቋሙ እንደወረደ በየጊዜው የምንታዘበው ነገር ነው :: ታዲያ ለተመልካቹ የታየው ግልፅ ነገር እንዴት ሆኖ ነው አሰልጣኙ ማየት የተሳነው ? አውቆ የተኛን ነገር ካልሆነ በስተቀር :: 90 ሚሊየን ህዝብን የሚወክል ብሔራዊ ቡድን በአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት ስር ሲወድቅ ግፍ ተንኮል ሸፍጥ ሲሰራ ዝም ብሎ ማየት ኧረ ተገቢ አይደለም ኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡ ኧረ የሰሚ ያለህ ! ኧረ የፌዴሬሽን ያለህ ! ኧረ የስፖርት ኮሚሽን ያለህ ! ኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡኡ

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!