የኮንጎው ዘማች በድል እንዲመለስ …
ህዳር 07, 2008

በይርጋ አበበ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ በእኛ አገር የሰዓት አቆጣጠር ከአብራጃው 12 ሰዓት በተጋጣሚው ጎንጎ ብራዛቢል የሰዓት አቆጣጠር ደግሞ 10 ሰዓት ላይ በስታዴ አፎንሶ ስታዲየም የሚጫወት ይሆናል። በዚህ ጨዋታ አሸናፊ የሚሆነው ቡድን ወደ 21ኛው የዓለም ዋንጫ ለሚደረገው ጉዞ ከሚፋለሙ የምድብ ተፋላሚዎች ይመደባል። ለዚህ ደግሞ ዋልያዎቹ ወደ ብራዛቢል ሲያቀኑ አንድ እድል ብቻ ይዘው ሲሆን እነሱን የሚገጥመው ባለሜዳው የጎንጎ ብራዛቢል ብሔራዊ ቡድን ግን አራት እድሎችን ይዟል። የዋልያዎቹ እድል ተጋጣሚያቸውን በሁለት ጎል ልዩነት አሸንፈው መውጣት ሲሆን ተጋጣሚያቸው ግን ማሸነፍ፣ አቻ መውጣት እና በአንድ ጎል ልዩነት መሸነፍም እድሎቹ ናቸው። ከዚህ በላይ ደግሞ የሚጫወተው በሜዳው በመሆኑ አራተኛ እድል ተደርጎ ሊወሰድለት ይችላል።

የዮሐንስ ሳህሌ ስብስብ ወደ ኮንጎ ያደረገውን ዘመቻ በድል አድራጊነት እንዲመለስ ምን ማድረግ አለበት? በሚል ርዕስ ላይ መጠነኛ ዳሰሳ የምናደርግ ይሆናል። ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ በዛሬው ጨዋታ የማይሰለፉ ተጫዋቾች ካሉም እንጠቁማለን። አብራችሁን ሁኑ።

ማጥቃት ማጥቃት አሁንም ማጥቃት እንደገና ማጥቃት

Ethiopia Vs Congo

ባሳለፍነው እሁድ አመሻሹ ላይ በካምቦሎጆ ጨዋታቸውን ያካሄዱት ሁለቱ ቡድኖች ሰባት ጎሎችን አስቆጥረው ጨዋታው በእንግዳው ቡድን አራት ለሶስት አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል። በእለቱ የዮሐንስ ሳህሌ ስብስብ በፈረንሳያዊው ክላውድ ሎሮይ ቡድን አራት ጎሎች ሊቆጠሩበት የቻለው አንድም በራሱ በተከላካይ መስመሩ ስህተት ወዲህ ደግሞ በግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት ድክመት ሲሆን በሶስተኛነት የሚነሳው ችግር ደግሞ የቡድኑ ወገብ የተሰበረ መሆኑ እንደነበረ ጨዋታውን የተመለከቱ ሁሉ ይስማማሉ።

አንድ አባባል ልጠቀምና ወደ ሀሳቤ ላምራ። “ብልህ ሰው ከሌላ ሰው ውድቀት ይማራል ሞኝ ደግሞ ከራሱ። የሞኝ ሞኝ ደግሞ ሳይማር መማሪያ ብቻ ይሆናል” ሶስተኛዋን የጨመርኳት እኔ ነኝ። ለዚህ አባባል አንድ አጋዥ ላክልበት። እወቅ ያለው በ40 ቀኑ አትወቅ ያለው በ40 ዓመቱ።

መቼም ልብ ያለው ሸብ ነው ይባላልና የአባባሌ ፍሬ ነገር ግልጽ ሳይሆንላችሁ አይቀርም። አባባሌ እንደ ባልቴት ሆኖ ነገሬን አስረዝሜ ከሆነ በግልጽ እንዳብራራው ይሁን። ብሔራዊ ቡድኑ በዛሬው ጨዋታ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት በርካታ መማሪያ መንገዶች በዙሪያው እንዳሉ ግልጽ ነው። እንዳለመታደል ሆኖ በእሁዱ ጨዋታ እኛ በመሸነፋችን ለዛሬው ጨዋታ ትምህርት የምንወስደው ከተጋጣሚያችን ሳይሆን ከራሳችን ይሆናል። እናም ባለፈው ጨዋታችን ምን ምን ስህተቶችን ገደፍን? ምንስ እናርም? ብሎ ወደ ሜዳ መግባት የአሰልጣኝ ታክቲካል ብስለት ነው። እናም በሜዳውና በ33 ሺህ ደጋፊው ፊት ለዚያውም አርቲፊሻል ሳር በተገጠመለት ሜዳ የሚገጥመን የኮንጎ ብሔራዊ ቡድን ካለፈው ጨዋታ በበለጠ በዛሬው ጨዋታ እንደሚፈትነን ለማወቅ ጠንቋይ መቀለብ የሚጠበቅብን አይሆንም።

ስለዚህ በዛሬው ጨዋታ ብሔራዊ ቡድኑ የጠበበ እድሉን እንዲያሰፋ እና በሜዳው የደረሰበትን ሽንፈት ለማወራረድ ባለው ጠንካራ ጎን ላይ ትኩረት አድርጎ ሊጫወት ይገባል። ጥያቄው ታዲያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጠንካራ ጎኑ የት ላይ ነው? የሚለው ይሆናል። እኔ እንደተመልካች እና እንደ ጋዜጠኛ የቡድኑ ጠንካራ ጎን ሆኖ ያየሁት ሁለት ነገሮች ላይ ነው። የመጀመሪያው ኳስ ይዞ መጫወት ሲሆን ሌላው ደግሞ እንደ ስዩም ተስፋዬ፣ ዋሊድ አታ፣ ሳላዲን ባርጌቾ እና ታሪክ ጌትነት አይነት ቡድንን መምራት የሚችሉ ልምድ እና ፕሮፌሽናልነት ያላቸው ተጫዋቾችን መያዙ ነው። እንዲሁም በተጠባባቂ ወንበር ላይ እንደ ዘካሪያስ ቱጂ አይነት ተጠባባቂን መያዙም ለጥንካሬው አንዱ ተጠቃሽ ሊሆን ይችላል። በተለይ የመከላከያው ነጂብ ሳኒ በእሁዱ ጨዋታ የሰራውን ተደጋጋሚ ስህተት ለተመለከተ ዘካሪያስ የት ሄደ ብሎ እንዲጠይቅ ያስገድደዋል።  

ብሔራዊ ቡድናችን ኳስ ይዞ የመጫወት ጠንካራ ባህል እና የበላይነት አለው ሲባል ቡድኑ ኳስን በመጣችበት መጠለዝ ወይም ለተጋጣሚ ቡድን በሚመች መንገድ ኳስን በርቀት መቀባበልን በመተው ኳሷን ተቆጣጥሮ መጫወትና የተጋጣሚን የግብ ክልል በተደጋጋሚ መፈታተን አለበት ለማለት ነው። በዚህ አካሄድ ኮንጎዎች የቱንም ያህል ጠንካራ የተከላካይ ምሽግ ቢቆፍሩ ከብዙ ሙከራ በአንዱ መቁሰላቸው በሌላኛው ደግሞ መድከማቸው አይቀርም። አዲስ አበባ ላይ የታየው የኮንጎ ቡድንም ቢሆን ጥንካሬው በመልሶ ማጥቃት እና ተደራጅቶ በመጫወት እንጂ ኳሷን በማስታመም በኩል የተካነ የኳስ አርቲስት ተጫዋቾች አልነበሩትም።  

ሌላው የቡድኑ ጥንካሬ አድርጌ የጠቀስኩት የተጫዋቾች ልምድና ፕሮፌሽናሊዝምነት ላይ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የተከላካይ መስመሩ ላይ ኳስን ይዞ መጫወት የሚወደውን ሳላዲን ባርጌቾን ከአስቻለው ታመነ ይልቅ ከዋሊድ አታ ጋር ማጣመር ከቻሉ የተከላካይ መስመሩን በሚገባ ማጠር ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም ዋሊድ እና ሳላዲን በጣምራነት ሲጫወቱ ያሳዩት ውህደት የአተር እና የባቄላ እንጂ የዱባ እና የቅል አይመስል ነበር። ዋሊድ ካለው የካበተ ልምድ እና ፕሮፌሽናሊዝም አስተሳሰብ ጋር ድፍረትና ጉልበትን ቀላቅሎ የሚጫወተው ጠንካራው ሳላዲን ባርጌቾ ቢጣመሩ መልካም ነው ሲባል ከሁለቱ ጎን ደግሞ አምበሉ ስዩም ተስፋዬ ካለው ልምድ እና ጠንካራ ስነ ልቦና ጋር ታሳቢ መደረግ አለበት።

ነገር ግን የተከላካይ መሰመሩ በዚህ መልኩ ቢታጠርም የቡድኑ ወገብ እንደባለፈው ከተሰበረ ተከላካይ መሰመሩ በታንክ ቢታጠርም ጎሎችን ከማስተናገድ ወደ ኋላ አይልም። ለዚህ ደግሞ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የቡድኑን የመሃል ክፍል በተለይም የአማካይ ተከላካይ ቦታውን ከጋቶች ፓኖም ይልቅ የመከላከያው በሀይሉ ግርማ ወይም ባባ እንዲይዘው ቢያደርጉ እና ለጋቶች ደግሞ ሌላ ሚና ቢሰጡት መልካም ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

ጋቶች ፓኖም ከኳስ ጋርም ሆነ ያለ ኳስ ያለው ብቃት ጥሩ የሚባል ቢሆንም የቡድኑን ተከላካይ ክፍል ሽፋን በመስጠት በኩል ግን የሚመሰገን አይደለም። ይህ የአማካይ ተከላካይ ቦታ ለቦታው ታማኝ የሆነ እና የተጋጣሚ ቡድን አጥቂዎችን በንስር አይን የሚከታተል ታጫዋች ካልተሰለፈበት በመልሶ ማጥቃት ፈጣን ወረራ የሚያካሂድ ቡድን የሚያደርሰውን ጥቃት መመልከት አይቻልም።

ለዚህም አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌም በዛሬው ጨዋታ በአማካይ ተከላካይ መስመሩን ቦታ ከጋቶች ይልቅ ለበሀይሉ የሚሰጡ ከሆነ መልካም ውጤት ሊመዘገብ ይችላል። ኳስ መያዝ፣ ተረጋግቶ መከላከል እና ጠንካራ የአጥቂ መስመርን መያዝ ዋልያዎቹ ከጎንጎ በድል እንዲመለሱ የሚያደርጋቸው ፎርሙላ ይሆናል።

የአጥቂ መስመሩን ማደራጀት

በእሁዱ የኢትዮጵያ እና የኮንጎ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ የታየው የዋልያዎቹ ሌላ ድክመት የአጥቂ መስመሩ ለተጋጣሚ ቡድን ተከላካይ ፈታኝ አለመሆን ነበር። ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው አዲሱ ፈረሰኛ ራምኬል ሎክ ከአሰላለፍ ውጭ በመሆኑ ነው። በዛሬው ጨዋታ እንደሚሰለፍ የሚጠበቀው የጋምቤላው ተወላጅ በመስመር በኩል የሚያደርገው ፍጥነትን የተላበሰ የማጥቃት ዘመቻ ዋልያዎቹን ለድል እንዲያልሙ ያደርጋቸዋል ብዬ አስባለሁ።

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ራምኬል ሎክን በዛሬው ጨዋታ መጠቀም ባይፈልጉ እንኳ በእሁዱ አሰላለፋቸው የተጠቀሙባቸው እነ በረከት ይሳቅ፣ ዳዊት ፈቃዱ እና አስቻለው ግርማ በተሻለ ሞራል እና ብቃት ሊመለሱ ይገባል። የኤልያስ ማሞ ከአሰላለፍ ውጭ መሆን ደግሞ የቀድሞ ብቃቱ ላይ የማይገኘውን ሽመልስ በቀለን ለተደጋጋሚ ስህተት ሲዳርገው የታየ ሆኗል። ለዚህም በዛሬው ወሳኝ ጨዋታ አንድም ያለውን አጠናክሮ መግባት ወዲህ ደግሞ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ የአሰላለፍ ለውጥ አድገው መጫወት ይኖርባቸዋል።

ጨዋታው ሊያመልጣቸው የሚችሉ

ወጣቱ የመሃል ተከላካይ አስቻለው ታመነ በጉዳት ምክንያት ላይሰለፍ እንደሚችል ይታመናል። የእርሱን ቦታ ደግሞ ለቱርኩ ጌንሸርቢሊ የሚጫወተው ዋሊድ አታ ተክቶ የሚሰለፍ ይሆናል። ሽመልስ በቀለም ቢሆን የጉዳት መጠኑ ስላልተረጋገጠ ላይገባ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

እንደ ምርቃት

በ2014 ብራዚል አዘጋጅተው በነበረው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የመጨረሻው የደርሶ መልስ ፍሚያውን ከናይጄሪያ ጋር ከማድረጉ በፊት የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ቡድን ጨዋታውን ያደረገው ከሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር ነበር። ሴንትራል አፍሪካዎች በአገራቸው የፖለቲካ አለመረጋጋት መፈጠሩን ተከትሎ የአገራቸው መሪዎች አመላቸውን እስኪያስተካክሉ እና እርቀ ሰላም እስኪያወርዱ ድረስ ብሔራዊ ቡድኑ ለዓለም እና ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን የሚያካሂደው ከሜዳው ውጭ ነበር። ምንም እንኳ የሰው ፊት እሳት ነው ቢባልም በአገራቸው መጫወት ያልቻሉት ሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊኮች ከዋልያዎቹ ጋር ያለባቸውን ጨዋታ እንዲያካሂዱ ደጅ የጠኑት የኮንጎ ብራዛቢልን ሲሆን ኮንጎዎችም እኛን ተማምናችሁ መጥታችሁማ አፍራችሁ አትመለሱም በማለት በራቸውን ከፍተው “ሜዳውም ፈረሱም ይሄው” ብለው ፈቀዱላቸው። ጨዋታውም ብራዛቢል ላይ ተካሄደ።

በዚያ ጨዋታ ዋልያዎቹ ሴንትራል አፍሪካን ማሸነፍ ካልቻሉ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ የሚችሉት ባፋና ባፋናዎቹ ነበሩ። እንደዚህ አይነት ከባድ ኃላፊነት እና ጠባብ እድል ይዞ የተጓዘው የሰውነት ቢሻው ስብስብ ከጎንጎ ዘመቻው የተመለሰው ተጋጣሚውን ሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክን ሁለት ለአንድ አሸንፎ በመውጣት ነበር። ዛሬስ?

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
JustThinkin [760 days ago.]
 Weldone Ethiofootball. The kind of article everyone should be wtriting and readuing before a crucial match like today. Then you can do the analysis once the dust settled. If only everyone is thinking like this, the team and managers would have l a great confidence and cencentration and wouldnt be thinking about what everyone would say if they lose. Great step in the right direction.

ዳንኤል [760 days ago.]
 አትጠረራጠሩ እነናሸንፋለን

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!