ከ17 ዓመት በታች ለሚካሄደው የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ውይይት ተካሄደ
ህዳር 08, 2008

በይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሚያካሂዳቸው የአገር ውስጥ ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው ከ17 ዓመት በታች የወንዶች እግር ኳስ ውድድር ላይ ዛሬ በኢትዮጵያ ሆቴል ውይይት ተካሄደ። በውይይት መድረኩ ከፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ተወካዮች የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ኮሚቴ የክለቦቹ ተወካዮች እና የጤና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የውይይት መድረኩ ያለፈውን ዓመት የውድድር ሂደት አጠቃላይ አካሄድ የተመለከተ ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በቀረበ ሪፖርትም የክለቦቹ ተወካዮች አስተያየታቸውን ሰጥተውበታል። ለተነሱ ጥያቄዎችም መልስ ተሰጥቶባቸዋል።

በፌዴሬሽኑ የውድድር እና ስነ ስርዓት ኮሚቴ የቀረበው ሪፖርት “የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው በ2006 ዓ.ም ሲሆን በወቅቱ የነበሩ ተሳታፊ ክለቦችም ስምንት ቡድኖች ብቻ ነበሩ። በስምንት ቡድኖች የተጀመረው ውድድርም በ2007 ዓ.ም በተጠናከረ ሁኔታ በመቀጠል ሁሉም በፌዴሬሽኑ ስር የፕሪሚየር ሊግ ውድድር የሚያካሂዱ ሁሉም ክለቦች የታዳጊ ወጣቶች እንዲኖራቸው በተሰጠው መመሪያ መሰረት 13 ክለቦች ተወዳዳሪ ሆነዋል” ሲል ያመለክታል። ሪፖርቱ አያይዞም 13ቱ ክለቦች በሶስት ምድብ ተከፍለው ውድድራቸውን ማካሄዳቸውን ይገልጻል። ባለፈው የውድድር ዓመት በታዳጊዎች ፕሪሚየር ሊግ ከተሳተፉት 13 ክለቦች መካከል ሀረር ከነማ እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዋናው የፕሪሚየር ሊግ ውድድር የሚሳተፍ ቡድን የሌላቸው ክለቦች ቢሆኑም በታዳጊዎች ፕሪሚየር ሊግ መሳተፋቸው አስመስግኗቸዋል።

በ2007 ዓ.ም በተካሄደው የታዳጊዎች የፕሪሚየር ሊግ ውድድርም አዳማ ከነማ የዋንጫ ባለቤት ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ከነማ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው ማጠናቀቃቸውን የገለጸው የፌዴሬሽኑ ሪፖርት ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ ክለቦች እንደየደረጃቸው 50 30 እና 20 ሹጨሺህ ብር ሽልማት ማበርከቱን ያትታል። ሀዋሳ ከነማ በአኘለ ሸጋነት የጸባይ ዋነጫ ተሸላሚ መሆኑንም አመልክቷል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ የታዳጊዎች ጥሎ ማለፍ አሸናፊ መሆኑ ተገልጿል።

በውይይት መድረኩ የተገኙ የክለቦቹ ተወካዮችም ባለፈው ዓመት በተካሄደው ውድድር እና በታዳጊዎች አያያዝ ዙሪያ አስተያየታቸውን አቅርበዋል። የፈረሰኞቹ ተወካይ “በኤም አር አይ ምርመራ ከአንዱ ክለብ የወደቀ ተጫዋች ስሙን ቀይሮ ለሌላ ክለብ ሲጫወት ይታያል ይህም የመሳሪያው ችግር ወይም የባለሙያዎች ለሙያቸው ታማኝነት አለመኖር ነው። የጸጥታ ሀይሉም በውድድር ቦታዎች ተገቢውን ድጋፍ ሲያደርግ አልነበረም” ሲሉ አቅርበዋል። ከሀዋሳ ከነማ የተወከሉት ደግሞ “ዳኞች በአገር እግር ኳስ ላይ የሚያሳርፉት ተጽእኖ ቀላል የሚባል አይደለም። ሆኖም የዳኞች ማህበር በታዳጊ ውድድሮች ላይ ጨዋታዎችን የሚመሩ ዳኞች ብቃታቸውን እንዲያሳድጉ ከዳኞች ማህበር የሙያ ማበልጸጊያ ስልጠና ሲሰጣቸው አይታይም። የጨዋታዎች መርሃ ግብርም ሊስተካከል ይገባል። ታዳጊዎቹ ጨዋታቸውን በአዘቦት ቀን ከማካሄድ ይልቅ የዋናው ቡድን ተጫዋቾች ውድድር በሚካሄድበት ቀን ከጨዋታው ቀደም ብሎ ባሉት ሰዓት ቢካሄድ ከታላላቆቻቸው ልምድ እና ተነሳሽነትን እንዲወስዱ ያግዛቸዋል። ከ17 ዓመት በታች ያሉ ቡድኖች በአገር አቀፍ ደረጃ የሊግ ውድድራቸውን የሚያካሂዱት እድሜያቸው 17 ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ብቻ ነው። እድሜያቸው 17 ከሞላ በኋላ ግን የሚወዳደሩበት ሊግ ባለመኖሩ ይበተናሉ። ይህ ደግሞ ክለቦችንም ሆነ ተጫዋቾቹን እየጎዳቸው ይገኛል” ሲሉ ተናግረዋል።

ከሀረር ከነማ የተወከሉት ደግሞ መገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች የታዳጊዎችን ውድድር እንደ ትርፍ አንጀት እንጂ እንደ ዋና ስራቸው ተመልክተው ትኩረት ሰጥተው አይዘግቡትም። የመጫወቻ ሰዓቱ 80 ደቂቃ ብቻ መሆን አይገባውም ዓለም አቀፉ መመዘኛ የሚያዘው 90 ደቂቃ ስለሆነ የእኛ ልጆችም 90 ደቂቃ እንዲጫወቱ መደረግ አለበት” በማለት ቃላቸውን ሰጥተዋል። የደደቢት ተወካዩ ደግሞ የውድድሩ ኮምዩኒኬ በወቅቱ አለመድረስ እና የስፖርታዊ ጨዋነት ጉዳይ ሊስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል።

በተደጋጋሚ ቅሬታ የቀረበበትን የተጫዋቾች እድሜ ተገቢነት የሚያሳውቀው “ኤም አር አይ መሳሪያ” ጉዳይ ሲሆን ለዚህ ጥያቄ መልስ የሰጡት ታዋቂው የስፖርት ጤና ባለሙያው ዶክተር አያሌው ጥላሁን ናቸው። ዶክተር አያሌው በመጀመሪያ ክለቦች በeኤም አር አይ ላይ እምነት አሳድረው ለተጫዋቾቻቸው ገንዘብ እየከፈሉ እድሜያቸውን ማስመርመራቸውን አድንቀው መናገር የጀመu ሩሰሩሆን “ከዚህ ዓመት ጀምሮ ግን በመሳሪያው ላይ ክለቦች ትልቅ እምነት ማሳደር እንዲችሉ በአገሪቱአሉ የተባሉ ሶስት ባለሙያዎች ተመድበው ስራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ ይገኛሉ” ብለዋል። በኤም አር አይ ተመርምረው እድሜያቸው ከሚፈለገው በላይ በመሆኑ የተባረሩ ተጫዋቾች ወደ ሌላ ክለብ ሂደው ስማቸውን እየቀየሩ ይጫወታሉ ለተባለው ቅሬታም ዶክተር አያሌው ሲመልሱ “ከዚህ ዓመት ጀምሮ ስጋት አይግባችሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

በ2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የታዳጊዎች ፕሪሚየር ሊግ ለመወዳደር ዝግጅቱን ሙሉ በሙሉ አጠናቆ የተጫዋቾቹን እድሜ በመሳሪያ አስመርምሮ ለጨዋታ ዝግጁ የሆነው ክለብ ሀዋሳ ከነማ ብቻ መሆኑን የገለጹት ዶክተር አያሌው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቡና ደደቢት ኤሌክትሪክ ባንክ ሲዳማ ቡና እና መከላከያ አብዛኞቹ ተጫዋቾቻቸው ምርመራውን አልፈዋል ብለዋል። ዳሽን ቢራ እና ሆሳዕና ከነማ በውድድሩ እንደማይሳተፉ መግለጻቸው ተገቢ አለመሆኑንም የህክምና ባለሙያው ገልጸዋል።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!