የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ታሪክ ክፍል ሶስት
ታህሳስ 02, 2008

ክፍል ሶስት

በይርጋ አበበ

በየሳምንቱ አርብ የሚቀርበው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ታሪክ የሚዳስሰውን ጽሁፋችንን ባለፉት ሁለት ሳምንታት በሴካፋ ዋንጫ ምክንያት አለማቅረባችን ይታወሳል። ሆኖም ከዛሬ ጀምሮ አምዱ በመደበኛነት እንደሚቀጥል እናሳውቃለን።

እግር ኳስ በኢትዮጵያ

በዚህ ንዑስ ርዕስ ስር የምናቀርበውን ጽሁፍ ያገኘነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ1961 ዓ.ም 25ኛ ዓመት የብር እዮቤልዩ በዓሉን ሲያከብር ካሳተመው መጽሔት ላይ ሲሆን የጽሁፉ ባለቤት ደግሞ ገዳሙ አብርሃ የተባሉ የእግር ኳስ እና የጽሁፍ ሰው ናቸው። የአቶ ገዳሙን ኀሳብም ሆነ ጽህፈት አንዳች ሳንገድፍ የምናቀርብ ይሆንና በመውጫችን አካባቢ ደግሞ የዚህ አምድ አዘጋጅ የራሱን ምልከታ ያክልበታል። አሁን ወደ ጽሁፉ!!  

፳፭ ዓመት እንኳንስ ለአንድ ድርጅት ለሰውም ቢሆን አጭር ዘመን በመሆኑ እግር ኳስ በኢትዮጵያ ባለፉት ፳፭ ዓመታት ያደረገው እርምጃ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። በእርግጥ በእነዚህ ፳፭ ዓመታት ውስጥ ብዙ ለውጥ አይተናል። እግር ኳስ በኢትዮጵያ እንደተጀመረ ዳኞቹ ጨዋታውን የሚዳኙት ፈረስ ተቀምጠው ሜዳው ላይ እየጋለቡ ነበር።

በዚያን ጊዜ የእግር ኳስ ተጫዋቾቻችን ግጭት የማያደርግ የለምና ጸብ ሲያነሱ ተመልካቹ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ዳኞቹ ጭምር ጸባቸውን እንዲያፋፍሙ ይገፋፏቸውና ያበረታቷቸው ነበር። በዚያን ጥሩ ዘመን ግብ ጠባቂዎች ቢሆኑ ኳሷን ለመያዝ ከፈለጉ መሬት ላይ መውደቅና መንደፋደፍ እንዳለባቸው መብታቸው ወይም ግዴታቸው መሆኑን መሆኑን አያውቁም ነበር። ብዙዎቹ የውጭ አገር ተመልካቾች እንደሚነግሩን የእኛ ሰው ጨቅጫቃ እና ነገር አጫሪ ነው ይላሉ። እውነታቸውን ሊሆን ይችላል። ይሁንና ይኸውም ጭቅጭቅ ብለሃል አላልኩም ነክተሃል አልነካሁም የሚለው ክርክር በኳስ ሜዳ ሲነሳ የጨዋታውን ደንብ እና ስነ ስርዓት ገና ያላወቁት የኳስ ተጫዋቾቻችን ዳኞችን ይሟገቷቸው ነበር። ዳኞችም ቢሆኑ እንዲያው ለስሙ ዳኞች ተባሉ እንጂ የሚዳኙትን ጨዋታ ሕግ እና ስነ ስርዓት በይሆናል ካልሆነ እነሱም አያውቁትም ነበርና ከጨዋታው ይልቅ የሁለቱ ወገኖች ንትርክ የበለጠ ትርኢት ሆኖ ይታይ ነበር።

አዎ ያ ጥሩ ዘመን አልፏል። ዛሬ የእግር ኳስን ህግና ስነ ስርዓት የሚያውቁት ዳኞችና ተጫዋቾች ብቻ ሳይሆኑ ተመልካቹም ቢሆን የደንብ አንቀጾች በመጥቀስ አንዳንድ አከራካሪ ነገር በተነሳ ጊዜ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ከመቋቋም አይመለሱም። ማለትም የቀድሞው ክርክር ጭቅጭቅ አለ። ፈረስ ላይ ተቀምጠው የሚዳኙት ዳኞች ግን ዓለም አቀፍ እግር ኳስ ድርጅቶች በሚያደንቋቸው ኢትዮጵያዊያን ዳኞች ተተክተዋል።

የግብ ጠባቂ ካስፈለገው መሬት ላይ ወድቆ ኳሷን መያዝ ህጉ አይፈቅድለትም ብለው በገነፈለ መንፈስ ይከራከሩ የነበሩት ተጫዋቾቻችን ዛሬ ለዓለም አቀፍ እግር ኳስ ደረጃ በደረሱ የመጨረሻውን ቴክኒክ ባጠናቀቁ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ተተክተዋል።

ህዝቡም ቢሆን ስለ እግር ኳስ ያለውን ፍቅር ለመገመት ከተፈለገ እነ ሪያል ማድሪድ እና ሳንቶስ ክለቦች እነ ፔሌ ዩዜቢዮ እና ጋሪንቻ በኢትዮጵያ ያላቸውን ዝና መጥቀስ ይበቃል። ከ፳፭ ዓመት በፊት በሣር ጎጆ ጽ/ቤቱን ያቋቋመው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ ለዓለም አቀፍ እና ለኦሎምፒክ ውድድሮች ተጫዋቾችን ያሰልፋል።
ከላይ የቀረበውን የአቶ ገዳሙ አብርሃን ጽሁፍ በደንብ ከተመለከትነው ከ1961 ዓ.ም በፊት እግር ኳስ በአገራችን ምን መልክ እንደነበረው ከመግለጽም ባለፈ ከ1961 ዓ.ም በኋላ እስከ አለንበት ዘመን ድረስ የእግር ኳሳችንን እድገት እንድንመለከት የሚያሳስብ የአዋቂ ምክር ያዘለ መልዕክት ሆኖ እናገኘዋለን።
በመጀመሪያ ደረጃ እግር ኳስ በኢትዮጵያ መካሄድ ሲጀምር ከነበረው ችግር አኳያ በአር ጊዜ ውስጥ ሊባል በሚያስችል ፍጥነት የእግር ኳሱ ደረጃ ሲያድግ ችግሮቹም በቀላሉ የተቀረፉ ይመስላል። እግር ኳስን በፈረስ ላይ ተቀምጠው ከሚዳኙ የጨዋታ ገላጋዮች ተነስቶ በአንድ ጊዜ የፊፋ እውቅና የተቸራቸውን ዳኞች አገራችን ማፍራት እንደቻለችም አቶ ገዳሙ ይገልጻሉ። ግብ ጠባቂ መሬት ላይ ወድቆ በእጁ ኳስ በመያዙ ምክንያት አምባ ጓሮ ይፈጥሩ ከነበሩ ተጫዋቾች ተነስቶ እንደ አሞራ ከግቡ ቋሚ እስከሌላኛው የግቡ ቋሚ የሚወረወሩ ግብ ጠባቂዎችን እስከማፍራት የደረሰ የእግር ኳስ እድገት እንደተፈጠረም ተገልጿል።

ታዲያ ይህ ጽሁፍ የሚያመለክተው አሁን በአገራችን ያለው የዳኝነት ደረጃ የግብ ጠባቂዎች ብቃት የተመልካች የኳስ ፍቅር እና የፌዴሬሽኑ ጥንካሬ ምን ይመስላል? የሚለውን ማየት ነው። እውነት ለመናገር በአቶ ገዳሙ አብርሃ ዘመን ስመ ገናና ከነበሩት እነ ሳንቶስ እና ሪያል ማድሪድ የመሰሉ ክለቦች እና እንደ ፔሌ ጋሪንቻ እና ዩዜቢዮ አይነት ተጫዋቾች በዘለለ በአሁኑ ወቅት እጅግ በጣም በርካታ የላቲን አሜሪካ እና የአውሮፓ እግር ኳስ ፈርጦችን ማየት የተለመደ ነው። በአርሴናል እና ማንቸስተር ዩናይትድ ፍቅር የተለከፈ የአገራችን እግር ኳስ ደጋፊ እንዳለ ቢሆንም ወደ አገር ውስጥ እግር ኳስ ስንመለከት ግን ተቃራኒው ሆኖ እናገኘዋለን።
ለአብነት አንድ አስረጅ ሁነት ለማቅረብ እንሞክር። በቅርቡ በአዲስ አበባ ተካሂዶ በነበረው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ አገሮች እግር ኳስ ውድድር በአዲስ አበባ ስታዲየም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሲጫወት ተመልካቹ መከታተል የቻለው አንድ ጨዋታ ብቻ ነበር ማለት ይቻላል። የዋንጫው ጨዋታ ደግሞ ጭራሽ በዝግ ስታዲየም የተካሄደ እስኪመስል ድረስ የስታዲየሙ ወንበሮች ባዶ ሆነው ታይተዋል። ስለዚህ በአሁኑ ወቅት እየተመለከትን ያለነው በውጤት ላይ የተመሰረተ ድጋፍ እንጂ እግር ኳስን ከልቡ በማፍቀር ስታዲየም የሚገባ ተመልካች ቁጥሩ ውስን መሆኑን ነው። ወደ አቶ ገዳሙ ጽሁፍ እንመለስ።

እግር ኳስ ከጦርነቱ በፊት

እግር ኳስ በኢትዮጵያ መቼ እንደተጀመረ በትክክል የሚያስረዱ ሰነዶችን ባለማግኜቴ ጣሊያን ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት የእግር ኳስ ጨዋታ ፈረስ በሚጋልቡ ዳኞች በሚዳኙበት ጊዜ ኳስ ይጫወቱ የነበሩትን አቶ ይድነቃቸው ተሰማን ሒጄ አነጋገርኳቸው። አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የባለ ፈረስ ዳኞችን ዘመን አልፈው ዘዛሬ የኢትዮጵያን አትሌቶች ወደ ኦሎምፒክ ለመምራት የበቁ ሰው ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝብ የስፖርት ፌዴሬሽን ረዳት ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የክብር ዋና ጸሀፊ የሆኑት አቶ ይድነቃቸው ከጣሊያን በፊት የነበረውን ሁኔታ እንዲገልጹልኝ ስጠይቃቸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሚጽፏቸውን የግል ማስታወሻዎች እንደገና ማንበብ አስፈልጓቸው ነበር።

የአቶ ይድነቃቸው ተሰማ እና የአቶ ገዳሙ አብርሃ ቃለ ምልልስ

እስቲ የቀድሞውን ታሪክ ያስታውሱን


ምንም እብኳን ተጽፎ የቆዬ ነገር ባይኖርም በዚያን ጊዜ የነበሩትን ሰዎች እየጠየቅሁ እንደተረዳሁት ፲፱፻፲፮ ዓ.ም ገደማ የውጭ አገር ሰዎች ማለትም Communities አርመኖች ህንዶች ግሪኮች እና ኢጣሊያኖች ቡድኖች እያቋቋሙ በጃን ሆይ ሜዳ እየተጠራሩ ግጥሚያ ያደርጉ ነበር። ከዚያ በኋላ የዳግማዊ ምኒልክና የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤቶች በልዩ ልዩ ደረጃ ቡድኖች እያቋቋሙ ከውጭ አገር ዜጎች ቡድኖች ገር ይጋጠሙ ነበር።እኔም በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ከገባሁበት ጊዜ ጀምሮ እንደማስታውሰው የትልልቆች ተማሪዎች ቡድን በጊዜው በተማሪ ቤታችን ሜዳ ከልዩ ልዩ ቡድኖች ሲጋጠም ትዝ ይለኛል።

በዚያን ጊዜ የነበሩትን እግር ኳስ ተጫዋቾች ያስታውሳሉ?

አዎ አንዳንዶቹን አስታውሳለሁ። በመጀመሪያ እነ መንበረ ያየህይራድ እነ በቀለ ማሙዬ በተለይም በቀለ ማሙዬ ኳሷን ወደ ሰማይ በመምታት እጅግ የታወቀ ስለነበረ አይዘነጋኝም። ከዚያ በኋላ ደግሞ የነበረውን ቡድን አሰላለፍ በሙሉ ባላስታውስም አንዳንዶቹን አልረሳቸውም።

ግብ ጠባቂው ደምሴ ሀይሌ ሲሆን ከጠላት በፊት አይሮፕላን ነጂ፣ ተከላካዩ ዘሪሁን ወጋየሁ፣ ዋቅጂራ ሰርዳ የመቶ ሜትር ሻምፒዮን ፈጣን ፯ ቁጥር፣ ደስታ ወልደየስ ግራ ክንፍ እሱም ከጠላት በፊት አይሮፕላን ነጂ ነበር። አብርሃ ደቦጭ በግራዚያኒ ጊዜ ቦንብ የወረወረው፣ ነጋ ኀ/ሥላሴ እነዚህ ሁሉ ነበሩ።

የጣሊያን ጦርነት ሊጀመር አቅራቢያ ደግሞ ከማስታውሳቸው ጥሩ ተጫዋቾች መካከል ስለሺ ድፋባቸው የምኒልክ ትምህርት ቤት ተጫዋች፣ ሯጭ፣ የዝላይ እና የጂምናስቲክ ሻምፒዮን ነበር። ከሁሉም ደግሞ የማደንቀውና የማልዘነጋው ተክለማሪያም ክፍሎምን ነው።  ተክለማሪያም ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የገባው ጠላት ኢትዮጵያን ከመውረሩ ከጥቂት ዓመታት በፊት ነበር። በገባ በ፲ኛው ቀን ኳስ እንደቀልድ ተላመደ። ሲራመድ ዘወትር በእጣቱ ይቆም ስለነበረ ሰውነቱ እንደማይከብደውና የላስቲክነት ባህሪይ ያለው ይመስል ነበር። በግራ እና በቀኝ ኳስ ይመታ ነበር።

የስዊድን ንጉሥ ልጅ ኢትዮጵያን ሊጎበኝ በመጣ ጊዜ በተማሪ ቤቶች መካከል በተደረገው ውድድር በ፻ ሜትር፣ በ፬፻  ሜትር፣ በ፩ሺህ ፭፻ ሜትር፣ በሽቅብ ዝላይ እና በዘንግ ውርወራ አንደኛ መውጣቱ ይታወሳል። ከነጻነት በኋላም እነደገና ለመጫወት ሞክሮ ነበር። ነገር ግን ዕድሜው እና ብዙ ጊዜ በማቋረጡ ሊረዳው አልቻለም።

በተለይ ደግሞ የግብ ጠባቂዎች አባት ብለን ልንጠቅሰው የምንችለው የተማሪ ቤታችን አስተዳዳሪ የነበሩት ብላታ ዳዊት እቁበእግዚእ ከአስመራ አስመጥተውት በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ይማር የነበረው ተስፋዬ አክልግን ነው። ተስፋዬ አክሎግ አስመራ ተጫዋች ስለነበረ ግብ ጠባቂ ተወርውሮ መሬት ወድቆ ኳስ መያዝ መቻሉን ያሳየን እሱ ነው። ከዚያ በፊት የነበረው ኳሱ በፊት በቀጥታ ከመጣ በእጅ በጎን ከሄደ እግርን ዘርግቶ እንጂ መውደቅ ጨርሶ አልነበረም።
ከዚህ በላይ ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ እና አቶ ገዳሙ አብርሃ ካደረጉት ቃለ ምልልስ መረዳት የቻልናቸው በርካታ አብይ ነጥቦች አሉ። በመጀመሪያ ደረጃ በአገራችን ያለው እግር ኳስን በተመለከተ የሚደረገው የመረጃ አያያዝ ክፍተትን ነው። በመረጃ ማጣት ምክንያት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ታላላቅ ሰዎችን በመጠየቅ በግል ማስታወሻቸው ላይ ያሰፈሩትን ነጥብ ለዘጋቢው ሲነግሩ እናነባለን። ይህ ባህል ደግሞ አሁንም በ21ኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኩል አለመቀየሩን እንመለከታለን።

ይቀጥላል!!

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!