ከ40 ቀናት እረፍት በኋላ የተመለሰው የኢትዮጵያ ሪሚየር ሊግ ሶስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዳሰሳ
ታህሳስ 04, 2008

በይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከ40 ቀናት መቋረጥ በኋላ ባሳለፍነው ቅዳሜ ጀምሮ ትናንት እሁድም ተካሂዷል። ሊጉ ለሁለት ሳምንትት በተካሄደው የሴካፋ ዋንጫ ውድድር ምክንያት ለ40 ቀናት መቋረጡን በርካታ የፕለጨሪሚየር ሊጉ አሰልጠጫኞች ተጫዋቾችና የእግር ኳስ ዘጋቢዎች እንዲሁም የክለብ አስተዳደሮች ሲወቅሱ መቆየታቸው ይታወሳል። ከሴካፋ ዋንጫ ውድድር መጠናቀቅ በኋላ የተጀመረው የ2008 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ባሳለፍነው ቅዳሜ ከቀትር በኋላ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ተካሂዶ የዋላ ሲሆን በማግስቱ እሁድም በአዲስ አበባ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች ተካሂደውበታል።

በአጠቃላይ ከሰባት የሊጉ ጨዋታዎች መካከል አምስቱ የደቡብ ክልል ክለቦች አስር ጎሎችን ሲያስቆጥሩ ስድስቱ የአዲስ አበባ ክለቦች ደግሞ ስምንት ጎሎችን አስቆጥረዋል። ድሬዳዋ ከነማ እና አዳማ ከነማ ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ጎሎችን አስቆጥረዋል። በአጠቃላይ በሶስተኛው ሳምንት መርሃ ግብር 21 ጎሎች መረብ ላይ ያረፉ ሲሆን ኤሌክትሪክ እና ዳሽን ቢራ ጎል ከተቆጠሩት 21 ጎሎች መካከል ምንም ድርሻ የሌላቸው ብቸኛ ክለቦች ሲሆኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ ደግሞ መረባቸውን ያላስደፈሩ ብቸኛ ክለቦች ሆነዋል።

በዚሁ የሶስተኛው ሳምንት መርሃ ግብር ሰባት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና ከአዳማ ከነማ እና አርባ ምንጭ ከነማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያደረጓቸው በተመሳሳይ አንድ እኩል በሆነ ውጤት የተጠናቀቁ ሲሆን ቀሪዎቹ አምስት ጨዋታዎች በመሸናነፍ ተጠናቅቀዋል። ሀዋሳ ከነማ እና ሆሳዕና ሀድያ ያካሄዱት ጨዋታ ደግሞ በሳመንቱ ከፍተኛ ጎል የተቆጠረበት ጨዋታ ሆኗል ሰባት ጎሎች ተቆጥረውበታል። ደደቢት መከላከያን ሶስት ለሁለት ያሸነፈበት ጨዋታም ሁለተኛው ከፍተኛ ጎል የተቆጠረበት ጨዋታ ሆኗል። ከዚህ በታች ደግሞ የኢትዮፉትቦል ዶትኮም ዘጋቢ በአዲስ አበባ የተካሄዱትን ሶስት ጨዋታዎች በዝርዝር ይተነትናቸዋል።
 
ኤሌክትሪክ ከቅዱስ ጊዮርጊስ

ፈረሰኞቹ ከኮረንቲዎቹ ያካሄዱት ጨዋታ የተጀመረው ከአመሻሹ 11 ሰዓት በኋላ ነው። በቅርቡ የአሰልጣኝ ሹም ሽር ያካሄዱት ፈረሰኞቹ በቅዳሜው ጨዋታቸው የተከላካይ ክፍላቸውን እንደተለመደው ጠንካራ አጥር ሰርተው የገቡ ቢሆንም በመጠኑም ቢሆን በግራ መስመር ክፍላቸው የመሃሪ መና ቦታ ክፍተት የታየበት ቦታ በመሆኑ በሁለተኛው 45 በአበባው ቡጣቆ ሊተካ ችሏል። የአማካይ ክፍላቸውን ደግሞ ከጠንካራው ተስፋዬ አለባቸው ጎን ተፈጥሯዊ የተከላካይ ተጫዋች የሆነውን አሉላ ግርማን ያሰለፉ ሲሆን የፈጣሪ አማካይ እጥረት ያለበትን ቦታ ምንያህል ተሾመ እና በሀይሉ አሰፋ እንዲሸፍኑት ለማድረግ ሙከራ ተደርጎ ነበር። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአቋሙ ላይ መሻሻል እያሳየ የመጣው ምንያህል ተሾመ የተሰጠውን አደራ በብቃት ለመወጣት ጥረት ያደረገ ቢሆንም በሀይሉ አሰፋ ግን የተጠበቀውን ያህል መንቀሳቀስ ሳይችል አምሽቷል።

ሌላው የአጥቂው ክፍል ነው። የአጥቂውን ክፍል እንዲመሩለት አደራ የጣለባቸው ለአንጋፋው አዳነ ግርማ እና ዩጋንዳዊው ብሪያን አሙኒ ሲሆን በተለይ አዳነ ግርማ በእለቱ ያባከናቸው የጎል እድሎች ፈረሰኞቹ ጨዋታውን ከእረፍት በፊት እንዳይጨርሱ አድርጓቸዋል። ከእረፍት በፊት ጥሩ የጎል እድል አግኝተው የነበሩት የፈረሰኞቹ አጥቂዎች ሁሉንም ከቋሚ ብረቱ ርቀት ላይ ስለሰደዷቸው እንጂ ጨዋታው ከእርፍት በፊት ብቻ ሶስት ለባዶ ማለቅ ይችል ነበር።

ኮረንቲዎቹ በበኩላቸው ሜዳ ላይ የሌሉ እስኪመስሉ ድረስ የሜዳውን አብዛኛውን ክፍል ለፈረሰኞቹ ትተውላቸው ራሳቸውን በውስን የሜዳው ክፍል ላይ ብቻ ወስነው ታይተዋል። ያም ሆኖ ግን በተለይ የቀድሞው የሙገር ሲሚንቶ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ የነበረው ፍጹም ገብረ ማርያም እና ናይጄሪያዊው ፒተር ንዋዱኬ ለፈረሰኞቹ የተከላካይ ክፍል መጠነኛ ጫና ለመፍጠር ሙከራ አድርገው ነበር።
ጨዋታው ከእረፍት መልሰ ሲቀጥል የአጨዋወትም ሆነ የተጫዋች ለውጥ አድረገው የገቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተጋጣሚያቸውብ የግብ ክልል ደጋግመው ማንኳኳት የቻሉ ሲሆን ጥረታቸው ተሳክቶላቸውም በአሊላ ግርማ አማካኝነት ማራኪ ጎል አግኝተው ጨዋታውን በዚሁ ውጤት በማጠናቀቅ ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዘው ወጥተዋል። የአሉላ ግርማ ጎል ከቅዱስ ጊዮርጊስ ደገጋፊዎችና የክለቡ አባላት በተጨማሪ በበርካታ የስፖርቱ ተከታታዮችም አድናቆት ተችሯታል።
 
በአጥቂ የተጨናነቀው አዳማ እና ያለ አጥቂ የገባው ኢትዮጵያ ቡና
ሁለቱ ቡድኖች ያካሄዱት ጨዋታ ደግሞ ትናንት ከቀትር በኋላ በእለቱ ሶስተኛው ሩብ ላይ የተካሄደ ነበር። እንግዳው ቡድን አራት አጥቂዎችን አሰልፎ የገባ ሲሆን በአንጻሩ ባለሜዳው ኢትዮጵያ ቡና ተፈጥሯዊ የሆነ አጥቂ ሳያሰልፍ በመስመር እና በመሃል አማካይ አጥቂዎች ነበር ወደ ሜዳ የገባው።

ከፍተኛ የመሸናነፍ ፉክክር እና የመሃል ሜዳ የኳስ ፍሰት በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በተለይ በቡናማዎቹ በኩል ወጣቱ እያሱ ታምሩ መስዑድ መሃመድ እና ኤልያስ ማሞ የፈጠሩት ጥምረት ድንቅ የነበረ ቢሆንም ሶስቱ ፈጣሪ አማካዮች የሚፈጥሩትን የጎል እድል በተጋጣሚ መረብ ላይ የሚያሳርፍ አጥቂ አለመኖሩ ቡናን ጎድቶት ታይቷል። በአዳማ ከነማ በኩል ደግሞ በዚህ የውድድር ዓመት ክለቡን ከወላይታ ድቻ የተቀላቀለው ብሩክ ቃልቦሬ ድንቅ ሆኖ ያመሸ ሲሆን በተለይም ጥቅጥቅ ብሎ የተደፈነውን የቡናን የአማካይ ክፍል ለማፈራረስ ያደረገው ጥረት በእጅጉ አስገራሚ ነበር። ከብሩክ ቃልቦሬ በተጨማሪ ደግሞ ታፈሰ ተስፋዬ እና ታከለ አለማየሁ እንዲሁም ግብ ጠባቂው ጃኮብ ፔንዜ ጥሩ የተጫወቱ የአዳማ ተጫዋቾች ነበሩ።

ከእረፍት በፊት ቡናዎች ያገኟቸውን የጎል እድሎች በብዛት ያመከነው ከሀላባ ከነማ ቡናን የተቀላቀለው ሳዲቅ ሽቶ ሲሆን አምበሉ መስዑድ መሃመድ እና የመስመር አጥቂው ጥላሁን ወልዴም ቢሆኑ ኳስና መረብን ማገናኘት እየቻሉ ግን ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ የቀሩ ተጫዋቾች ናቸው። በተለይ በቴኳንዶ ስፖርት የጥቁር ቀበቶ ባለቤት የሆነው ሳዲቅ ሽቶ ግን በርከት ያሉ ያለቀላቸው ኳሶችን ማግባት እየቻለ ማግባት ባለመቻሉ ከደጋፊውም ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶበታል።

ቡናዎች ከእረፍት መልስ ሳዲቅ ሽቶን አስወጥተውያቡን ዊሊያምን በማስገባት ጨዋታውን ይበልጥ ለማፍጠን ሲሞክሩ አዳማ ከነማዎች በበኩላቸው ምርጡን ተጫዋቻቸውን ታከለ አለማየሁን አስወጥተው ሚኬኤል ጆርጆን በማስገባት ይበልጥ ተዳክመው ታይተዋል። ይህ የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ድርጊትም መነጋገሪያ ሆኗል። ከዊሊያም ያቡን ተቀይሮ መግባት በኋላ ጨዋታውን አፍጥኖ የተጫወተው ቡና ጥሩ የጎል ማግባት እድሎችን መፍጠር ችሎ ነበር። ሆኖም በቡና አጥቂዎች ድክመት እና በአዳማ ከነማው ግብ ጠባቂ ፔንዜ ጥንካሬ ኳሶቹ ማረፊያቸውን መረቡ ላይ ማድረግ አልቻሉ።

ጨዋታው በከፍተኛ ውጥረት እየተካሄደ ባለበት ሁለተኛው አጋማሽ መገባደጃ አካባቢ ባሉት ቀሪ 15 ደቂቃዎች ላይ ግን የእለቱን ብቸኛ ቢጫ ካርድ የተመለከተው ጋቶች ፓኖም ከቡድን አጋሩ የተቀበለውን ኳስ ለአዳማ ከነማው ብሩክ ቃልቦሬ በማቀበል ትልቅ ስህተት ሰራ። ብሩክ ከጋቶች የተቀበለውን ኳስ ለታፈሰ ተስፋዬ አመቻችቶ በማቀበልም ታፈሰ ተስፋዬ የመጀመሪያዋን ጎል እንዲያስቆጥር አደረገ። ይህ የጋቶች ስህተት ከዚህ ቀደምም በብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች የታየ ቢሆንም የትናንቱ ስህተቱ ግን ቡድኑን ዋጋ አስከፍሎታል።
ከጎሏ መቆጠር በኋላ ውጤት ለማስጠበቅ የተጫወቱት አዳማ ከነማዎች በተለይ ተከላካያቸው ሞከስ ታደሰ በሰራው ስህተት ምክንያት ቡናዎች የአቻነት ጎላቸውን አግኝተዋል። ጎሏን ያስቆጠረው ደግሞ ጋቶች ፓኖም ነው።

ደደቢት ከመከላከያ የሳምንቱ ድንቅ ጨዋታ

ይህ ጨዋታ ያለምንም ጥርጥር በሳምንቱ ከተካሄዱ ጨዋታዎች ውስጥ ድንቅ የኳስ ፍሰት የታየበት ጨዋታ ነበር ማለት ይቻላል። አምስት ጎሎች የተቆጠሩበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አንድም ተጫዋች የቢጫ ካርድ ሰለባ ያልሆነበት ሲሆን ወደ ተጋጣሚ የጎል ክልል ደጋግሞ በመቅረብም ቢሆን ሁለቱም ክለቦች ጥሩ ነበሩ።

“እንደ ሳሙኤል ሳኑሚ አይነት ተጫዋች በቡድኔ ውስጥ ቢኖር ዋንጫ ለማንሳት እጫወት ነበር” ሲሉ ከወራት በፊት አስተያየታቸውን የሰጡት የቡናው አሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች ሲሆኑ የአሰልጣኙ አስተያየት ምን ያህል ትክክል እንደሆነ ሳሙኤል ሳኑሚ በትናንቱ ጨዋታ አሳይቷል። እንደ ቡና የአጥቂ ድርቅ አሰልጣኙ ሳኑሚን ቢመኙትም ናይጄሪያዊው አጥቂ ግን ለደደቢት አሁንም ጎል ማምረቱን ተያይዞታል። ትናንት ደደቢት ካስቆጠራቸው ሶስት ጎሎች መካከልም ሁለቱን በማግባት የቡድኑ አለኝታነቱን አሳይቷል። ቀሪዋን ጎል ደግሞ ዳዊት ፈቃዱ አስቆጥሯል። በመከላከያ በኩል የተቆጠሩትን ሁለት ጎሎች አምበሉ ሚካኤል ደስታ እና ወጣቱ አጥቂ ምንይሉ ወንድሙ አስቆጥረዋል።  

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
ቦቸራ [728 days ago.]
 አዳማዬዬዬ

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!