የኢትዮጵያ እግር ኳስ ምስቅልቅሎሽ
ታህሳስ 05, 2008

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ፣ ሚዲያውና ተጨባጭ እውነታዎች

አቤል ዓለማየሁ
myabel25@gmail.com

ሳቅ በሚያጭሩ ቃላት ንግግራቸውን በማጀብ የሚታወቁት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ዋሊያዎቹን እየመሩ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው መድረክ በመመለሳቸው ሳቢያ የአገራችን እግር ኳስ መነቃቃት አሳይቷል። ወደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ዓይናቸውን መወርወር ‹‹የሚጠየፉ›› ወገኖቻችን ሳይቀሩ ‹‹ክስተቱ›› ብርታት ሆኗቸው ወደ ካምቦሎጆ ጎርፈዋል። እንቅልፋሙ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገንዘብ ባይሠራበትም ‹‹ጮሌ›› ነጋዴዎች ወደ አገር ቤት ያሾለኳቸውን መለያዎች ብዙሐን ተሽቀዳድመው ለብሰዋል። ተስፋ ሰጪ እና የተሻለ እንቅስቃሴ ካለ እግር ኳሱ ገንዘብ ማምጣት እንደሚችል በሁነቱ ተስበው የመጡ ስፖንሰር አድራጊዎችም ማመላከቻ ናቸው።

ይህ የአንድ ሰሞን እግር ኳሳዊ ስኬት፣ ያመጣልን በጎ ጎኖች ቢኖሩትም ለብዙዎች የተዛባ አረዳድ ምክንያትም ሆኗል። ከአንዳንድ የቀድሞ የፌዴሬሽን አመራር አካላት አንስቶ በርካቶች በአፍሪካ ዋንጫው ድግስ መገኘታችንን ለእግር ኳሳችን መመንደግ እንደማሳያ አቅርበውታል። ለራሳችን የሰጠነው ግምት ከፍተኛ እንዲሆን ስላደረገንም ከአፍሪካ ዋንጫው በኋላ የውጤት ምስቅልቅል ሲገጥመን ተገቢ ያልሆነ የውጤት ንፅፅሮሽ ውስጥ እየከተተ በቁጣ ‹‹እንዴት?›› ያስብለንም ጀምሯል። ሳንሠራ ቁጣችን እየቀደመ ነው።

የሊጉ ደረጃ

የአገራችን እግር ኳስ ቀዳሚ ውድድር በሆነው 'የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ' ላይ ለሁለት ሲዝን ብቃታቸውን ጠብቀው የሚጓዙ ተጨዋቾችን ማግኘት በጨለማ ቤት ውስጥ ጥቁር ድመት የመፈለግ ያህል አስቸጋሪ ነው። በአቶ ሰውነት ቢሻው መሪነት በ2013ቱ አፍሪካ ዋንጫ ላይ የተሳተፉ ተጨዋቾች በአሁን ሰዓት በሊጉ ያላቸው ብቃት ምን ያህል እንደሆነ ጠይቆ መልስ መፈለግ እውነታውን ያመላክታል። ጥቂቶቹ ተጨዋቾች ‹‹ከዚህ በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ የኢትዮጵያ ታሪክ ተዘጋ›› ብለው የደመደሙ ይመስል፤ ከደቡብ አፍሪካ መልስ ጠፍተዋል ደረጃቸው ዝቅ ብሏል። የወቅቱ የብ/ቡድኑ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ቡድኑን ከተረከቡ ጊዜ ጀምሮ በሰባት ወር ውስጥ እንኳን የጠሯቸው በሊጉ ላይ ተስፈኛ እንቅስቃሴ ያሳዩ የነበሩ ተጨዋቾች ከብቃታቸው ጋር መዝለቅ ባለመቻላቸው በገቡበት በር 'መውጫ' ተቆርጦላቸው ተሸኝተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የክለቦችን የገንዘብ አቅም በእጅጉ ይፈትናል። ተጨዋቾች ከፊፋ ደንብ ውጪ ከ200 ኪሎ ሜትር በላይ የየብስ ጉዞ አድርገው ስለሚጫወቱ በሜዳ ላይ ይዳከማሉ። ለወደ ፊቱ ተስፋ ሰጪ የስታዲየም ግንባታ እንዳለ ቢታይም እስካሁን የነበሩት ብዙዎቹ የክልል ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳዎች ምቹ አለመሆን የተጨዋቾችን አቅም አላሽቋል።
ቅ/ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ከመግባት በላይ ረዥም ዓላማን ሰንቀው የሚጓዙ ተጨዋቾች ቁጥር አንጀት የሚያርስ ስላልሆነ የተጨዋቾቻችን ትኩረት የመሳብ ጊዜን ያሳጥረዋል። መለያ እየቀያየሩ ኪሳቸውን የሚሞሉበት ጊዜ ስለመጣም ብሔራዊ ቡድን መመረጥ እና ተፅዕኖ መፍጠርን ለመሳሰሉ ገፊ ምክንያቶች እንዲጨነቁ አያደርጋቸውም።

የአሰልጣኞች ዘመናዊ ስልጠናን የማግኘት እና የመስጠት አቅምም እንደ ብዙ የአገራችን የሙያ ዘርፎች ሁሉ ጎዶሎ ነው። የሚሰጡ ሥልጠናዎች የግለት Intensity መጠን ተቀራራቢ ባለመሆኑ ሳቢያ ተጨዋቾች ወደ ብ/ቡድን ሲመጡ የአሰልጣኞች ራስ ምታት ይሆናሉ። አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በዚህ ይፈተኑ እንደነበር ገልፀው ያውቃሉ። አሰልጣኝ ዮሐንስም ከዚህ ያመልጣሉ ብሎ ማሰብ አይቻልም።

በዚያ ላይ አሰልጣኞቻችን በየጥጋጥጉ መተቻቸት እንጂ ተጋግዘው መሥራትን አልተካኑበትም። ከመጋረጃ ጀርባ እርስ በርስ መጎነታተል ብቃት ቢሆን ሁሉም የ‹‹ፕሮፌሰርነት›› ማዕረግ በተቀቡ ነበር።   

የዮሐንስ ፈተና እና ሚዲያው

ፕሪምየር ሊጉ በተዳከመበት፣ ያልተቋረጠ ብቃት የሚያሳዩ ተጨዋቾች እጥረት ባለበት በዚህ ሰዓት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አለቅነት በእሺታ የተቀበሉት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ኃላፊነቱን ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ አወዛጋቢነታቸው እንደቀጠለ ነው። ከቦታው ይገባቸዋል/አይገባቸውም የጀመረው ክርክር፣ በድኅረ ጨዋታ በሚሰጡት ተናዳፊ እና አስማሚ ያልሆኑ መግለጫዎች፣ የተጨዋቾች ምርጫ ዝርዝርና የቡድን አጨዋወት ቅንጅት ማነስ ዙሪያ ወጣ ገባ እያለ ሰውዬውን ዋነኛ የትኩረት አጀንዳ አድርጓቸው ሰንብቷል።

አሰልጣኝ ዮሐንስ በቡድናቸው ውስጥ የራሳቸውን ቀለም ማኖር እንደፈለጉ ሙከራቸው ይናገራል። በታዳጊ እና ወጣት ቡድን ውስጥ መለያ አጥልቀው ወደ ስታዲየም አምርተው የማያውቁ ተጨዋቾችን በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ ከማካተትም አልፈው የዋና ተሰላፊነትን ሚና ሰጥተዋቸው ታይተዋል። እንደ አስቻለው ታመነ ዓይነት የማይገረሰስ ማገር፣ እንደ አንተነህ ተስፋዬ ዓይነት ተጨማሪ የመከላከል ኃይል፣ እንደ ተካልኝ ደጀኔና ቢንያም በላይ ዓይነት ተስፈኛ ጠቃሚ ተጨዋቾችን ለቡድኑ አበርክተዋል።

አሰልጣኙ ለቡድኑ ከገቡት ቃል ኪዳን የመጀመሪያው ለቻን ማሳለፍ የሚለውን ያሳኩ ሲሆን፣ ለጋቦኑ የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ መሳለፍ ደግሞ የሚጠብቃቸው ትልቁ የቤት ሥራቸው ፈተናቸው ነው። ቡድኑ በሴካፋ ያሳየውን አሰልቺ እና ቅንጅት አልባ እንቅስቃሴ የተመለከቱ የእግር ኳስ ቤተሰቦች ዮሐንስ የጋቦኑን ትኬት መቁረጥ የሚያስችል አቅም ቡድናቸው ላይ እንደሌለ በመጠቆም አምርረው ተችተዋቸዋል። በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ፡፡ በዚህ ዓመት በስፖርቱ ክበብ እግራችን እስኪቀጥን ብንጓዝ የእኚህን አሰልጣኝ ያህል ያወዛገበ እና የትችት ናዳ የወረደበት ሰው ፈልጎ ማግኘት አይቻልም።

አቶ ዮሐንስ ከጋዜጠኞች ጋር ሲገናኙ ዲፕሎማት መሆን አልቻሉም። ለጥያቄ ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት አሊያም ለመልስ ከመቆጠብ ይልቅ ‹‹አንተ ማን ስለሆንክ ነው እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ የምትጠይቀኝ?›› ዓይነት ተናዳፊ መልሶች በመሰንዘር አላስፈላጊ ንትርክ ገጥመዋል። ብልሐት በተሞላበት መንገድ ሕዝብ እና መገናኛ ብዙሐን የሚፈልጉትን እየሰጡ መሸኘት ሲችሉ ሕዝብን የሚያስቆጡ አመርቃዥ ቃላት በመሰንዘራቸው ከውጤት ማጣት በኋላ በአዲስ አበባ ስታዲየም ለደረሰባቸው ውግዘት አስተዋፅኦ አለው። በቅርብ የሚያውቋቸው ዮሐንስ በአንድ ለአንድ እና በቡድን ውይይት ወቅት ያላቸውን አፍ የሚያስከፍቱ ምላሾች ከጋዜጠኞች ፊት ሲቀመጡ እንዳጡት ይናገራሉ። ምናልባትም አንዳንድ የሚዲያ ባለሙያዎች አፍ ላይ በሚፈጠሩ ያልታሰበባቸው እና ምክንያዊ ያልሆኑ አሉታዊ ትችቶች ስለሚሰላቹ 'ሚዲያ ሩም' ውስጥ ቁጡ እንደሚያደርጋቸው መገመት ይቻላል። 

አሉታዊ ትችት መሰንዘር ‹‹የአንቱታን ካባ ያስደርባል›› የተባለ ይመስል በአሁን ሰዓት የበረከቱ የኢትዮጵያ ስፖርት ሚዲያ ባለሙያዎች በዚህ ተጠምደው ይታያሉ። ወፍ በጩኸቷ ንጋትን ከማብሰሯ በፊት በሬዲዮ ሞገዶች ሾልከው ወደ ቤታችን በመምጣት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን እና አሰልጣኙን ከፍ ዝቅ ሲያደርጓቸው እናደምጣለን። ጋዜጠኞቹ በአሰልጣኙ ምላሾች ሆድ ስለሚብሳቸው ምሽጋቸው በሆነው ሚዲያቸው ላይ፣ ጥይት ሳይቆጥቡ ከፍተኛ የተኩስ እሩምታ በማዝነም የመልስ ምት ይሰጣሉ።

ከትችቶቻቸው መሀከል ግርምትን የሚጭርብኝ ‹‹ሌሴቶ ለምን ተገዳደረችን?፣ ከሲሸልስ ጋር እንዴት ነጥብ እንጋራለን? ሳኦቶሜ እና ፕሪንስፔ ሜዳዋ ላይም ቢሆን እንዴት ታሸንፈናለች? ሱማሌ ላይ እንዴት ሁለት ጎል ብቻ እናስቆጥራለን?›› ዓይነት ራስን በተሳሳተ ሚዛን ላይ የሚያስቀምጡ እና ማሰላሰል የተሳናቸው አስተያየቶች ናቸው። እውነት እንነጋገር ከተባለ የእኛ እግር ኳስ ከሱማሌ ፈቀቅ እንዲል ምን ያህል ሠርተንበት ነው ሁለት ብቻ ጎል ስላገባን ቁጭት የሚገባን? የትኛው ቀጣይት ያለው የእግር ኳስ ሥርዓት ዘርግተን ነው በሳኦቶሜ እና ፕሪንስፔ ስለተሸነፍን ፀጉር የምንነጨው? ሁለት የውድድር ዘመን በቅጡ የምንመካባቸው ተጨዋቾች ሳናበቃ ከሲሸልስ ጋር ነጥብ መጋራታችን እንዴት የሳምንት የሬዲዮ የውይይት ርዕስ ይሆናል? ሌሴቶ በሜዳችን ስታስጨንቀን ‹‹እንዴት?›› ብለን ቁጡ ከመሆናችን በፊት ከእኛ የተሻለ ሠርታ እንደመጣች ምን ያህል ፈትሸናል?

አሁን ላይ በታሪክ ብቻ መኖር አይቻልም። ዛሬ የእግር ኳስ የመሸናነፍ ደረጃ ጠቧል። ሱማሌን 18 ለ 1 ያሸነፍንበት ዘመን ዛሬም ይደገም ብሎ ማለት ሰዓት ወደኋላ ይቆጥራል ብሎ እንደማሰብ ነው። የእግር ኳሷ ታላቅ አገር ብራዚል እኮ በ2014 በደገሰችው የዓለም ዋንጫ ውድድር በጀርመን 7 ለ 1 ተሸንፋለች። ጀርመን ይህን ድል ያገኘችው በረዥም ዓመት የሥራ ውጤት ነው። እኛ ግን ሳንሠራ ጩኸታችን አድማስ ጥግ ደርሷል። በየሚዲያው ሽንፈታችንን እየፐወዝን ‹‹እንጀራ ማብሰያ›› እያደረግነው ነው። አንዳንድ ጋዜጠኞች በሚፈለገው ደረጃ ብሔራዊ ቡድኑ ከሚዲያው የሚፈልገውን እገዛ ነፍገውታል።

በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ዘመን ሕዝቡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላይ ከፍተኛ የእኔነት ብሔራዊ ስሜት ያሳይ ነበር። በሰውነት እግር በተተኩት በፖርቱጋላዊው ማሪያኖ ባሬቶ ጊዜ መጠኑ እያነሰ መጥቶ በአቶ ዮሐንስ ጊዜ በቡድናቸው ጥራት ማነስ፣ ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾች ትተው በወጣቶች ቡድናቸውን ማጨቅ ቁጣን በሚያጭሩ አስተያየታቸውና በተለያዩ ምክንያቶች ሕዝቡ ላይ መቀዛቀዝ ታይቷል፡፡ ቡድኑ በአዲስ አበባ ስታዲየም ቁጥሩ ባነሰ ተመልካች ፊት ጨዋታ ማድረጉ ለዚህ ማሳያ መሆን ይችላል፡፡ እዚህ ላይ የሚዲያው ቆስቋሽነት አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡

እየሳሳ የመጣውን የእኔነት ስሜት ለመመለስ እና ቡድኑን ትኩረት ሳቢ ለማድረግ አሰልጣኙ በቀጣይ ጊዜያት በሜዳ ውስጥም ሆነ ከሜዳ ውጪ በጥንቃቄ መሥራት አለባቸው። በሚፋጀው ወንበር ላይ የተቀመጡት የቡድኑን ደረጃ እያወቁ ስለሆነ ከተጠያቂነት አያመልጡምና በቀጣይ ጊዜያት ከሚዲያ ጋር አተካሮ የሚገጥሙበትን ጊዜ ቡድናቸውን ለቻን ለማቀናጀት ይጠቀሙበታል ብዬ ገምታለሁ።

ሕዝቡ የሚፈልገው የዮሐንስ እና የሚዲያውን አተካሮ እና ሰበብ መስማት ሳይሆን የእግር ኳሱን ትንሳዔ ማየት ነው። የክለቦች በጀት ዘመን ያለፈባቸው ተጨዋች መሰብሰቢያ እና የግለሰቦችን ኪስ ማደለቢያ ከመሆን ነፅቶ ለነገ የሚጠቅሙን ሕፃናት ላይ በትጋት መሥራት ይገባል። ሚዲያው ይህ ተፈፃሚ እንዲሆን ብሔራዊ ቡድኑን እና አሰልጣኙን ከሚተችበት ጊዜ በላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ ይገባዋል። የአውሮፓ ልሂቅ አሰልጣኞች ተደራጅተው ብሔራዊ ቡድናችን ላይ ቢሠሩ ምስቅልቅል ውስጥ ያለውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቀጣይነት ላለው ስኬት ያበቁታል ብዬ አላስብም። የቻን ዋንጫ ብንበላ፣ ለአፍሪካ ዋንጫ ብናልፍ እግር ኳሳችን መሠረት ስለሌለው ነገ ተመልሶ እዚያው ነው የሚረግጠው። እናም መሠረቱን ሳንሠራ በቤቱ የቀለም ምርጫ ላይ ፀብ በመግጠም ዘመናችንን አናገባድ።


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Bedlu Mekonen [732 days ago.]
 Good alalysis. Nice article I hope the media operators learn a lot from this article.

JustThinkin [732 days ago.]
 Finally, non-emotional unbiased article from Ethiofootball. This is the kind of opinion I would like to read from most sports media. Congratulations Ethiofootball for realising the systematic and long satanding problem with Ethiopian football in general and the national game in particular. I hope now everyone stops scape-goating a single person as the main and only cause of the problem and start looking into how things can be addressed at grass-roots, club and federation level. Weldone once again EF. Keep up the good work. Proud of you.

tanoo [731 days ago.]
 Appreciable, Very sensible professional observation/ criticism. Most importantly the article pointed out a number of key relevant facts related to the staggering problems of our football development ,the media and the spectators. the junk media usually ignores these facts I think mainly because of lack of understanding of the real issue and lack of original thought. If not for all of them, for most of the media stars the subject matter is incomprehensible if it should take to analyze it in broader way beyond its current status or a single game. That is why we are listening every day an overused phrases and opinions. I hope this article encourages the main actors at EFF, football strategist to look in to the real problem from different perspective and develop a clear grand strategy that can be understood and debated by everybody.

Gizegeta [730 days ago.]
 @ ethiofootball.com ለምንድነው የምንሰጣቸው ኮመንቶች delete የሚደረጉት ? ከብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ጋር ከተጋጫችሁ ጀምሮ ስለ አሰልጣኙ የምንሰጣቸውን አስተያየቶች ሳንሱር እያደራጋችሁት ነው:: ምንድነው ችግራችሁ ? እኛ ደጋፊዎች የተሰማንን ስሜት ያየነውን ስህተት በጨዋነት መናገራችን ምኑ ላይ ነው ክፋቱ ???

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!