የአራተኛው ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ውሎ
ታህሳስ 09, 2008


በይርጋ አበበ

የኢትየጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለ40 ቀናት ተቋርጦ ከተጀመረ በኋላ ያለፈውን የእረፍት ጊዜያት ለማካካስ ይመስላል ክለቦች በየ 40 ሰዓት ልዩነት እንዲጫወቱ እየተደረገ ነው። ከሳምንት ሳምንት ብቃቱን ወጥነት ባለው መልኩ ጠብቆ መጫወት የሚችል ተጫዋች የለውም እየተባለ የሚተቸው የአገራችን ትልቁ ሊግ በየሰበብ አስባቡ እየተቋረጠ እንደገና ደግሞ ከቆመበት እየቀጠለ መካሄዱ ክለቦችን በፋይናንስም ሆነ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች እየጎዳ ነው ሲሉ ደጋግመው ቢናገሩም ሰሚ ካጡ ቆይተዋል። ለምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ተብሎ ለ40 ቀናት ተቋርጦ የነበረው ሊግ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ደግሞ በድጋሚ ለ44 ቀናት እንደሚቋረጥ ቀደም ብሎ እርሙን አውቆታል። ለማንኛውም ሊጉ በድጋሚ ለ44 ቀናት ከመቋረጡ በፊት እየተካሄደ መሆኑ በራሱ “በጀ” የሚያስብል ነው ብሎ ማለፍ ይቻላል።

ትናንት ሀሙስ እና ረቡዕ በአዲስ አበባ አራት ጨዋታዎችን እና በክልል ደግሞ ሶስት ጨዋታዎችን ያካሄደው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ውድድር ከዚህ በታች ያለውን መልክ ይዞ ተጠናቋል።

ፈረሰኞቹ ከጸሀይ መውጫው ጋር

በእድሜ አንጋፋ የሊጉን ዋንጫ ደጋግሞ በማንሳትም ቀዳሚ የሆኑት ፈረሰኞቹ በዚህ ሳምንት መርሃ ግብር ጨዋታቸውም የፀሀይ መውጫውን ክለብ በሜዳቸ አስተናግደው አንድ ለባዶ በሆነ ውጤት ማሸነፋቸውን ዝግጅት ክፍላችን በቀጥታ የጨዋታ ውጤት መከታተያ አምዱ መግለጹ ይታወሳል። ናትናኤል ዘለቀ ከ18 ክልል ውጭ አክርሮ የመታት ኳስም ከቀድሞው የፈረሰኞቹ ግብ ጠባቂ ሳምሶን አሰፋ መረብ ላይ ማረፍ የቻለች ብቸና ኳስ ነበረች።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች እንደተለመደው ሮበርት ኦዶንካራን በግቡ ቋሚ መሃል ያቆሙ ሲሆን ከዩጋንዳዊው ፊት ለፊት ያለውን ቦታ የያዙት ደግሞ አምበሉ ደጉ ደበበ ከአይዛክ ዩሴንዴ ዘካሪያስ ቱጂ እና አለማየሁ ሙለታ ነበሩ። አራቱ ተከላካዮች የፈጠሩት ጠንካራ ጥምረት ቀድሞውንም የተጋጣሚን የግብ ክልል መድፈር የሚያሳፍረውን የድሬዳዋ ከነማን አጥቂ ክፍል በቀላሉ መቆጣጠር ችለውበታል።

ከአራቱ የፈረሰኞቹ ተከላካዮች በተጨማሪ ደግሞ በተደጋጋሚ ጊዜ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞችን ለትችትና ለመገናኛ ብዙሃን ለውዝግብ የሚዳርጋቸው ተስፋዬ አለባቸው ወይም ቆቦ በመሀል ሜዳው ላይ እንደፈለገው ይፈነጭበት ነበር። ተስፋዬ አለባቸው ካለው ወቅታዊ ምርጥ ብቃት አኳያ እንኳንስ በቦታው ምንም ተጫዋች ላልያዘው የዋልያዎቹ ስብስብ ለየትኛውም አፍሪካዊ ብሔራዊ ቡድን ይመጥናል እየተባለ በሚነገርበት በዚህ ወቅት ከድሬዳዋ ከነማ ጋር ፈረሰኞቹ ሲጫወቱ እንደተጠበቀው የእለቱ ኮከብ ሆኖ ውሏል።

ብቸኛዋ ሴት አሰልጣኝ የምትመራው ድሬዳዋ ከነማ የቀድሞውን የቡናዎቹን አምበልና ተወዳጅ ተጫዋች ዳዊት እስጢፋኖስን ለመጀመሪያ ጊዜ በማሰለፍ የመሀል ሜዳውን የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ለመያዝ ቢሞክርም የዳዊትን ድካም የሚያግዝ ተጫዋች ባለመኖሩ ዳዊት እስጢፋኖስ በእለቱ የባከነ ሰው ሆኖ አምሽቷል።

በአጠቃላይ ግን ድሬዳዋ ከነማ በእለቱ ሶስት ያለቀላቸው ኳሶችን ቢያገኝም የተጋጣሚ ቡድንን መረብ መድፈር የሚፈሩት አጥቂዎች ያገኟቸውን ኳሶች በሙሉ ለሮበርት ኦዶንካራ አስታቅፈውታል። በፈረሰኞቹ በኩል ደግሞ አዳነ ግርማ ብቻውን አራት የጎል እድሎችን ቢያገኝም የጎሉን መስመር ማየት ተስኖት ሁሉንም ኳሶች አድራሻቸውን ከመረቡም ከግብ ክልሉም ውጭ አድርጓቸዋል።

የዳኝነት ስህተት ጎልቶ የታየበት የባንክ እና የዳሽን ጨዋታ

የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ ደረጃ በየጊዜው እየቀነሰ እንዲሄድ ምክንያት ተደርገው ከሚጠቀሱት አካላት መካከል ዳኞች ይገኙበታል። ይህ አባባል ምን ያህል ትክክለኛ እንደሆነ ረቡዕ አመሻሽ ላይ ንግድ ባንክ እና ዳሽን ቢራ ሲጫወቱ በትክክል ተረጋግጧል። ዳሽን ቢራዎች በኳስ ቁጥጥርና አጠቃላይ የጨዋታው ስልተ ምት ላይ የበላይ ሆነው ባመሹበት ጨዋታ የአሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማሪያም ልጆች አመሀ በለጠ በጨዋታው የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል ማሸነፍ ችለዋል።

በሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በአሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋ የሚሰለጥኑት ጎንደሬዎቹ ለተመልካች አዝናኝ ጨዋታን ከማሳየታቸውም በላይ የተጋጣሚያቸውን የግብ ክልል ደጋግመው መፈተን ችለው ነበር። በንግድ ባንክ በኩል ደግሞ ጎሏ ከተቆጠረችበት ደቂቃ ጀምሮ ያሉትን ቀሪዎቹን 80 ደቂቃዎች ሰዓት ለማባከን ያደረጉት ሙከራ የጨዋታውን ጣዕም ያጠፉት ከመሆኑም በላይ ክለባቸውን ለአምስት ሺህ ብር ቅጣት ዳርገውታል። ሰዓት ለማባከንና ያገኟትን አንዲት ጎል ሳይበትኑ ቋጥረው ለመውጣት ባደረጉት ሙከራ አምስት ተጫዋቾች የቢጫ ካርድ የተመለከቱ በመሆኑ ንግድ ባንክ የአምስት ሺህ ብር ቅጣት ይከናነባል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ሆነ የዳኞች ማህበር በዳኝነት ጉዳይ ከፍተኛ ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ የተስተዋለበት ጨዋታ ነበር። በዚህ ሳምንት ከታዩ ጉልህ የዳኝነት ስህተቶች አኳያ የዳኞች ብቃት ወዴት እያመራ እንደሆነ በግልጽ የታየበት ሳምንት በመሆኑ በዚህ ጉዳይ የሚመለከታቸው አካላት የቤት ስራውን ወስደው ሊሰሩ ይገባል።

ማሸነፍ የተሳነው መከላከያ

መከላከያ እግር ኳስ ክለብ የፊታችን የካቲት በሚጀመረው የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፍ ቢሆንም በፕሪሚየር ሊጉ እያሳየ ያለው አቋም ግን “ወፌ ቆመች” እየተባለ ለመቆም እንደሚውተረተር ህጻን ልጅ አይነት ሆኗል። በፕሪሚየር ሊጉ ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ አሸንፎ በቀሪዎቹ እየተሸነፈ እና ነጥብ እየጣለ መጓዙን ገፍቶበታል። ታናንትም በአዲስ አበባ ስታዲየም ከደቡብ ክልሉ አርባ ምንጭ ከነማ ጋር ተጫውቶ የአርባምንጭ ከነማው ትርታዬ ደመቀ በ24ኛው ደቂቃ ባስቆጠረበት አንድ ለባዶ ሲመራ ቆይቶ በጨዋታው መገባደጃ አካባቢ ምንይሉ ወንድሙ ባስቆጠራት ጎል ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።

መከላከያ ትናንት ካሳየው የወረደ አቋም አኳያ ነጥብ ተጋርቶ የማይገባው ቢሆንም “እንዲሁ ከመቅረት የገንፎ እንጬት ላስ” እንዲሉ አበው አንድ ነጥብ ማግኘት መቻሉም እንደ ድል ሊቆጠርለት ችሏል። በዚህ ጨዋታ እንግዳዎቹ ከሜዳቸው ውጭ ተጫውተው ያገኟትን የአንድ ጎል አድቫንቴጅ ለመጠቀም በመፈለጋቸው ሰዓት ለማባከን ባይሞክሩ ኖሮ ተጨማሪ ጎሎችን ማስቆጠር ይችሉ ነበር።

በመከላከያ በኩል ምንይሉ ወንድሙ እና በሀይሉ ግርማ በአርበምንጭ ከነማ በኩል ደግሞ ታደለ መንገሻ እና አምበሉ በረከት ቦጋለ ጥሩ ሲጫወቱ ታይተዋል።

ኤሌክትሪክ በድጋሚ የተሸነፈበት ጨዋታ

የሳምነቱ የመጨረሻ መርሃ ግብር የተካሄደው ትናንት አመሻሹ ላይ ሲሆን ተጋጣሚዎቹ ደግሞ ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነው። “ኢትዮጵያዊያን ግብ ጠባቂዎች ለምን ከግቡ ቋሚ ብረቶች መሃል እንደሚቆሙ አይገባቸውም” እየተባሉ በተደጋጋሚ ጊዜ ይተቻሉ። የትናንቱ የኢትዮጵያ ቡናው ወንድወሰን ገረመው ለዚህ አባባል ትክክለኛነት ማሳያ ሊሆን ይችላል። ጨዋታው በተጀመረ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ናይጄሪያዊው ፒተር ኒዋድኬ ከግቡ ክልል በግምት ከ35 ሜትር በላይ ርቆ ወደ ጎል የላካትን ኳስ መያዝ ያልቻለው የቡናው ግብ ጠባቂ ኤሌክትሪኮች መሪ እንዲሆኑ በር ከፍቶላቸዋል።

ከጎሏ መቆጠር በኋላ ተጭነው የተጫወቱት የአሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች ልጆች ዮሴፍ ደሙዬ የኤሌክትሪክ ተከላካዮችን አሞኝቶ ካለፋቸው በኋላ ያሻገረለትን ኳስ ያቡን ዊሊያም ክለቡን አቻ ማድረግ ችሏል። ያቡን ዊሊያም ከዚህ ጎል በተጨማሪም በኤሌክትሪክ ተከላካዮች ተጠልፎ በመውደቁ ፍጹም ቅጣት ምት ለክለቡ አስገኝቶ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያ ከዩጋንዳ በሴካፋ ዋንጫ በመለያ ምት ሲለያዩ መለያ ምቱን ያባከነው ጋቶች ፓኖም ትናንትም ቡድኑ ያገኘውን ፍጹም ቅጣት ምት ለኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ አሰግድ አክሊሉ አስታቅፎታል። ጋቶች ፍጹም ቅጣት ምት ከማምከኑም በላይ ቡና በመሃል ሜዳ የጨዋታ የበላይነት እንዲወሰድበት አስተዋጽኦ አድርጎ ነበር።

ኤሌክትሪኮች በትናንቱ ጨዋታ ከፒተር ንዋድኬ እና አዲሱ ነጋሽ ውጭ ሌላ ተጫዋች ይዘው የገቡ ባልመሰሉበት ጨዋታ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾችን በሀይል አጨዋወት ለማቆም ሲሞክሩ ታይተዋል። አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሀይል አጨዋወት ለመጫወት የሞከሩት ኮረንቲዎቹ ከእረፍት መልስ ይበልጥ የተከላካይ መስመራቸው ለተጋጣሚ ቡድን ተጋላጭ ሆኖ ነበር። በተለይ ዮሴፍ ደሙዬ አከታትሎ ያባከናቸው ሁለት የጎል እድሎች ከታለመላቸው ዓላማ ላይ ቢውሉ ኖሮ ቡና አራት ለአንድ ማሸነፍ ይችል ነበር።

የቡናን የማሸነፊያ ጎል ያስቆጠረው ያቡን ዊሊያም ሲሆን ለጎሏ መገኘት በእለቱ ምርጥ ሆነው ያመሹት መስዑድ መሀመድ ኤሊያስ ማሞ እና እያሱ ፈጠነ የነበራቸው ድርሻ ከፍተኛ ነው። በእለቱ በቡና በኩል ከሶስቱ አማካዮች በተጨማሪ የተከላካይ መስመር ተጫዋቾቹ ጠንካራ ጥምረት ፈጥረው የነበረ ቢሆንም የግብ ጠባቂው ጉዳይ ግን የክለቡ ትልቅ የቤት ስራ ሆኗል። ባሳለፍነው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ለባዶ የተሸነፈው ኤሌክትሪክ ትናንትም በድጋሚ የንፈት ጽዋውን ለመጎንጨት ተገድዷል።

ታፈሰ ጎል ማምረቱን ሲቀጥል ሆሳዕና ሃድያ አንድ ነጥብ አገኘ

ታፈሰ ተስፋዬ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ ከ120 በላይ ጎሎችን ለተለያዩ ክለቦች በማስቆጠር ታሪክ ያለው ተጫዋች ነው። በዘንድሮው የፕሪሚየር ሊግ ውድድርም በአራት ጨዋታዎች አራት ጎሎችን በማስቆጠር ኮከብ ጎል አግቢነቱን ገና በጊዜ ተያይዞታል። ታፈሰ ትናንት ጎል ያስቆጠረው ክለቡ አዳማ ከነማ በሜዳው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ደደቢትን አስተናግዶ ሶስት ለሁለት ባሸነፈበት ጨዋታ ሲሆን ለአዳማ ከነማ ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠረው ወጣቱ ቡልቻ ሆራ ነው። አንዷን ያስቆጠረው ደግሞ ታፈሰ ተስፋዬ ነው። ቡልቻ ሆራ ባለፈው የውድድር ዓመት ከአዳማ ከነማ ከ17 ዓመት በታች ቡድን የውድድሩ ኮከብ ጎል አግቢ እና ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ከተመረጠ በኋላ የዋናው ቡድን ተጫዋችነት እድል የተሰጠው ወጣት ነው።

ደደቢት ሶስድት ለሁለት ይሸነፍ እንጂ ከሜዳው ውጭ ተጫውቶ ተጋጣሚውን በያሬድ ዝናቡ የቅጣት ምት ጎል መምራት ችሎ ነበር። ደደቢት ከያሬድ ዝናቡ በተጨማሪ በዳዊት ፈቃዱ አማካኝነት አንድ ጎል አስቆጥሮ ነበር።

ትናንት ከተካሄዱ አምስት ጨዋታዎች መካከል ሁለቱ በደቡብ ክልል የተካሄዱ የደቡብ ደርቢዎች ነበሩ። አራቱ ተደቡብ ክልል ክለቦች እርስ በእርስ በተገናኙበት የትናንት ጨዋታቸው ሶስት ጎሎችን ብቻ ያስቆጠሩ ሲሆን ቦዲቲ ላይ ወላይታ ድቻ ፕሪሚየር ሊጉን ከተቀላቀለ በኋላ አሸንፎት የማያውቀውን ሃዋሳ ከነማን አስተናግዶ በፈቱዲን ጀማል ብቸኛ ጎል በማሸነፍ በሀዋሳ ከነማ ላይ ያላውን የበላይነት አስጠብቋል።

ሆሳዕና ላይ የተካሄደው የሆሳዕና ሃድያ እና የሲዳማ ቡና ጨዋታ አንድ እኩል በሆነ ውጤት ተጠናቋል። ሁለቱ ቡድች መሳ ለመሳ የተለያበትን ውጤት እንዲያስመዘግቡ ጎሎችን ያስቆጠሩት አሸናፊ ይታየው ለባለሜዳው ሆናዕናሀድያ ሲሆን ለእንግዳው ሲዳማ ቡና ደግሞ ላኪ ላበርዲያን ነው። ውጤቱን ተከትሎም ሆሳዕና ሀድያ ከሶስት ጨዋታ ተከታታይ ሽንፈት በኋላ የመጀመሪያ አንድ ነጥብ ያገኘበት ሳምንት ሆኗል።


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Daniman [795 days ago.]
 በተደጋጋሚ ጊዜ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞችን ለትችትና ለመገናኛ ብዙሃን ለውዝግብ የሚዳርጋቸው ተስፋዬ አለባቸው ወይም ቆቦ በመሀል ሜዳው ላይ እንደፈለገው ይፈነጭበት ነበር። ተስፋዬ አለባቸው ካለው ወቅታዊ ምርጥ ብቃት አኳያ እንኳንስ በቦታው ምንም ተጫዋች ላልያዘው የዋልያዎቹ ስብስብ ለየትኛውም አፍሪካዊ ብሔራዊ ቡድን ይመጥናል እየተባለ በሚነገርበት በዚህ ወቅት ከድሬዳዋ ከነማ ጋር ፈረሰኞቹ ሲጫወቱ እንደተጠበቀው የእለቱ ኮከብ ሆኖ ውሏል። long live for Tesfaye Alebachew ( Kobbo ) tnx ethiofoot ball you well said !

felexsami [795 days ago.]
 ተስፋዬ አለባቸው ኢትዮጵያዊው ያያ ቱሬ

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!