አንዳንድ ነጥቦ ስለ ፈረሰኞቹ እና 80ኛ ዓመት የምስርታ በዓላቸው
ታህሳስ 10, 2008


በይርጋ አበበ

የአፍሪካን እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የመሰረቱት እና ለረጅም ዓመታት ያገለገሉት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ፣ ኢትዮጵያ ሶስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ስታነሳ የውድድሩ ኮከብ ጎል አግቢ የነበረው መንግስቱ ወርቁ፣ ኢትዮጵያ በ1982 ዓ.ም የሴካፋን ዋንጫ ስታነሳ ጨዋታውን በቀጥታ በሬዲዮ ሲያስተላልፍ የነበረው ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ በተደጋጋሚ “ገብሬ የመታውን ገብሬ የመታውን….” እያለ የጠራው ገብረ መድህን ሀይሌ፣ በ1994 ዓ.ም ሩዋንዳ ኪጋሊ ላይ እና በ1997 ዓ.ም እዚሁ አዲስ አበባ ላይ የሴካፋን ዋንጫ ኢትዮጵያ ስታነሳ ቡድኑን ያሰለጠነው አስራት ኃይሌ፣ የወቅቱ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች ዮሃንስ ሳህሌ እና ፋሲል ተካልኝ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በደርግ መንግስት አስገዳጅነት ክለቡም ውለታው ተረስቶ እንዲፈርስ ሲደረግ “ገላዬ ከዚህ ማሊያ ውጭ የማንንም ክለብ ማሊያ መልበስ አይችልም” ብሎ ራሱን ከእግር ኳስ ያገለለው ስዩም አባተ፣ አሁን በስደት እንግሊዝ አገር የሚገኘው ስንታየሁ ጌታቸው ቆጬ፣ ታታሪው ግራኛ ተከላካይ ዳዊት መብራቱ ገዳዳው፣ የወቅቱ የአገራችን ውድ ተጫዋች ሳላዲን ሰይድ እና ሌሎች በዚህ ክፍል ስማቸው ተዘርዝሮ ሊያልቅ የማይችል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ለብሰውት የተጫወቱት ማሊያ ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ።

የቅኝ ግዛት ምኞት ናላውን ያዞረው ፋሽሽቱ ቤኒቶ ሞሶሎኒ አባቶቹ አድዋ ላይ የደረሰባቸውን ውርደት ቀልብሶ ኢትዮጵያን በድጋሚ በቅኝ ግዛቱ ስር ለማድረግ በቁሙ እየቃዠ በነበረበት ወቅት፣ ድንጋይ ዳቦ ነበር እየተባለ በሚተረትበት ዘመን፣ ስለ ቀንዳም ፈረስ በሚነገርበት በዚያ የስልጣኔ ነገር በማይታሰብበት ዘመን 1928 ዓ.ም፣ የአፍሪካ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ገና ከአንድ መንደር ያነሰ የቆዳ ስፋት እና በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እየኖረባት በነበረበት ዘመን፣ ኢትዮጵያ አውሮፕላን ባልነበራት ዘመን፣ አየለ አትናሼ እና ጆርጅ ሉካስ የተባሉ ወጣቶች በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያውን ኢትዮጵያዊ ክለብ አቋቋሙ። ያ ክለብ ነው ዛሬ በአጠቃላይ ከ55 በላይ ዋንጫዎችን መደርደሪያው ላይ የሰቀለው፣ በአገሪቱ እግር ኳስ ታሪክ የመጀመሪያው የካፍን መመዘኛ አግኝቶ የተመዘገበው፣ ያ ክለብ ነው የጋናውን ሀያል ክለብ ኸርትስ ኦፍ ኦክን አራት ለባዶ በማሸነፍ ምድረ ጋናዊያንን ያሸማቀቀው።

ከላይ የተገለጹትን መገለጫዎች አንስተን የገለጽነው ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ዘንድሮ የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት እያከበረ ይገኛል። የአንድ አዛውንት እድሜን ያስቆጠረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘንድሮ የምስረታ በዓሉን እንዴት ነው የሚያከብረው? ለሚለው ጥያቄ የክለቡ አመራሮች የተናገሩት ቃል አለ። ያንን ቃላቸውንም ዛሬ ከዚህ በታች አስቀምጠነዋል።

የፈረሰኞቹ ዋና ጸሀፊ አቶ ሰለሞን በቀለ፣ የክለቡ የስራ አመራር ቦርድ ዋና ጸሀፊ አቶ ንዋይ በየነ እና የክለቡ የምስረታ በዓል አስተባባሪ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ አቶ ቀጸላ ሙላት በግዙፉ ሸራተን አዲስ ሆቴል በአንደኛው የመሰብሰቢያ አዳራሽ መድረክ ላይ በክብር ተቀምጠዋል። የክለባቸውን ታሪክ እጅግ በመጠኑ ካቀረቡ በኋላ ስለ በዓሉ አከባበር ማብራሪያ በመስጠት መድረኩን ከጋዜጠኞች ለሚነሱላቸው ጥያቄዎች ክፍት አደረጉት። ከ30 የማያንሱ ጋዜጠኞች የተገኙበትን መግለጫ የመሩት የፈረሰኞቹ አመራሮችም ከጋዜጠኞች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጡባቸው። እኛም ከጥያቄዎቹ መካከል የተመረጡትን ከእነ መልሶቻቸው አቅርበናቸዋል።

ክለቡ ከተመሰረተ 80 ዓመት ሞልቶታል። ይህም ታላቅ ድል ነው በውጤት በኩል ካየነውም ስኬታማ ነው ማለት እንችላለን። ነገር ግን ክለቡ የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት ሲያከብር “የኔ ነው የሚለው ቅርሱ ምንድን ነው?” ሲል የመጀመሪያው ጥያቄ ቀረበ። ለዚህ ጥያቄ በቀጥታ መልስ የሰጡት አቶ ሰለሞን በቀለ ናቸው። አቶ ሰለሞን ሲመልሱ “ጊዮርጊስ የኔ የሚለው ሀብቱ እና ቅርሱ ህዝቡ ነው” በማለት የጀመሩ ሲሆን “ነገር ግን ቁሳዊ ሀብትን በተመለከተ ክለቡ እንደ ተቋም አደረጃጀቱን በየጊዜው እያሻሻለ በመሄድ በአሁኑ ሰዓት የራሱ ጽ/ቤት፣ ሆስቴል፣ መለማመጃ ሜዳ እና በአገሪቱ እግር ኳስ ታሪክ ከክለቦች የመጀመሪያ የሚያደርገውን የታዳጊዎች ማሰልጠኛ ማዕከል ባለቤት ነው። ነገር ግን ይህ በቂ ስላልሆነ ወደፊትም የኔ የሚለው ሀብት ይኖረዋል ሲሉ መለሱ።

የምስረታ በዓላችሁን ስትገልጸጹልን የአካዳሚ ግንባታው መጠናቀቁን ገልጻችሁልናል። ነገር ግን ስለ ስታዲየሙ ያላችሁት ነገር የለም። የስታዲየሙ ግንባታ ምን ደረጃ ላይ ደረሰ? ሁለተኛው ጥያቄ ነው። ሁለቱ ሀላፊዎች ማለትም አቶ ንዋይ እና አቶ ሰለሞን ሲመልሱ “የስታዲየሙ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ተጠናቅቆ ታዩታላችሁ። በዚህ መድረክ ላይ ስለ ስታዲየሙ ምንም ያላልነው ቦታው እና ጊዜው ስላልሆነ ነው” አሉ።

ክለቡ 80ኛ ዓመቱን እንደሚያከብር ቀደም ብሎ ሲናገር ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች እንደሚያካሂድ ገምተን ነበር እሱም ሆኗል። ነገር ግን ጥር 1 ቀን እና ጥር 5 ቀን የምታደርጉት ኢንተርናሽናል ጨዋታ ከተገመቱት ክለቦች በታች ደረጃ ያላቸው ናቸው። ለምን እነዚህን ክለቦች ጠራችሁ? የሚል ጥያቄ ተጠየቁ። ለዚህ ጥያቄ የተሰጠውን ምላሽ በትናንትናው ዝግጅታችን ስላቀረብነው በድጋሚ ማቅረቡን ስላልወደድነው ከትናንትናው ዝግጅት እንድታነቡት ጋብዘን ወደ ቀጣዩ ጥያቄ እና መልስ እናመራለን።

የብስራት ስፖርት አዘጋጁ ጋዜጠኛ መንሱር አብዱል ቀኒ ሶስት ጥያቄዎችን የጠየቀበና የክለቡን አመራሮችም የፈተኗቸው ጥያቄዎች ደግሞ የሚከተሉት ናቸው። “አየለ አትናሼ እና ጆርጅ ሉካስ ይህንን ክለብ ባይመሰርቱት ኖሮ ምናልባት እኛም እዚህ ላንገኝ እንችል ይሆናል። ክለቡ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ብዙ ስራዎችን የሰራ ቢሆንም እነዚህን መስራቾች ግን የምናስታውስበት መታሰቢያቸው ምንድን ነው?” የሚለው የመጀመሪያው ነው። ቀጣዩ የመንሱር ጥያቄ ደግሞ “ከጠላት ወረራ በፊት ጀምሮ የተቋቋመው ክለባችሁ በጠላት ወረራ ጊዜ በአገሪቱ የሚዘመሩ ብሔራዊ ኩራትን የሚቀሰቅሱ መዝሙሮችን የሚዘምሩት የናንተ ልጆች ነበሩ። አሁንስ ይህንን የአገር ፍቅር ለአዲሱ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ምን እየሰራችሁ ነው?” የሚለው ሲሆን የመጨረሻው ጥያቄ ግን “የይድነቃቸው ተሰማ መተታሰቢያ የሆነው የክለቡ ታዳጊዎች ማሰልጠኛ ማዕከል ለበዓሉ ማድመቂያ ሆኖ ይመረቃል። አካዳሚው ሲመረቅ መቼም ሜዳውና ግንቡ ብቻ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም የማሰልጠኛ ማንዋሎችም እንደተዘጋጁ እገምታለሁና ስለ ማንዋሎቹ ይዘት ብትነግሩን” የሚለው ነው።

እነዚህን ጥያቄዎች በጥንቃቄ አድምጠው መልስ የሰጡት አቶ ንዋይ እና አቶ ሰለሞን ሲሆኑ እንዲህ ብለዋል። ለመጀመሪያው ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ። “የእነ አየለ እተናሼ እና ጆርጅ ሉካስ መታሰቢያን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ ልክነህ እንደታሰበው መታሰቢያ የላቸውም። ነገር ግን ክለባችን ሁለቱን ባለታሪኮች የሚያስታውስበት ፕሮግራም አለው። በመጀመሪያ ትንሹን መታሰቢያቸውን ልንገራችሁ በበዓሉ ላይ የሚካሄዱት የክለቡ አባላት ጨዋታ በእነሱ ስም ነው። ትልቁን መታሰቢያቸውን ግን ትንሽ ጠብቁን ጊዜው ሲደርስ ይፋ እናደርጋለን” ሲሉ መልስ ሰጥተውበታል። ለሁለተኛው ጥያቄ መልስ ሲሰጡም “የጊዮርጊስን ታሪክ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ዶክመንት እስካሁን አልተሰራም ነበር። አሁን ግን የክለቡን የ80 ዓመት ጉዞ በተገቢው መጠን ሊገልጽ የሚችል መጽሃፍ እና ዘጋቢ ፊልም እያዘጋጀን ነው። ይህ የታሪክ ቅብብሎሹን በተገቢው መጠን እንዲካሄድ ያደርጋል ብለን እናስባለን። በዚህ በኩል እናንተም ጋዜጠኞች መረጃዎችን ለህዝብ በማድረስ በኩል ድርሻ አላችሁ” ብለዋል።

የአካዳሚውን ግንባታ ምረቃ እና የማንዋል ዝግጅቱን በተመለከተ ሲመልሱ ግን የሚመረቀው ሜዳው እና ቤቶቹ ብቻ እንጂ የማሰልጠኛ ማንዋል እንዳልተዘጋጀ የተናገሩ ሲሆን አካዳሚው ግን ስራውን የሚያከናውነው በአውሮፓ ደረጃ መሆኑን ተናግረዋል።


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!