ፕሪሚየር ሊጉ በአምስተኛው ሳምንት ያስተናገዳቸው አብይ ክስተቶች
ታህሳስ 13, 2008


በይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአምስተኛ ሳምንት መርሃ ግብሩ አዳዲስ ክስተቶችን አስተናግዶ ማክሰኞ አመሻሽ በኢትዮጵያ ቡና እና በቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ተጠናቋል። በዚህ ሳምንት ከተካሄዱ ሰባት ጨዋታዎች መካከል አንድ ጨዋታ ብቻ ማክሰኞ አመሻሽ ላይ ሲካሄድ ቀሪዎቹ ስድስት ጨዋታዎች የተካሄዱት ሰኞ እለት ነበር። አምስቱ ጨዋታዎች ከአዲስ አበባ ውጭ ሲካሄዱ ሁለቱ ብቻ ማለትም ኮረንቲዎቹ ከደደቢት እና ቡናማዎቹ ከፈረሰኞቹ ያካሄዷቸው ጨዋታዎች ብቻ ናቸው አዲስ አበባ ላይ የተካሄዱት። ለመሆኑ ፕሪሚየር ሊጉ በዚህ ሳምንት ምን አዲስ ነገር ነበረው? እነማን ተሳካላቸው? እነማንስ ስኬት እንደ ጉም በነነባቸው? የሚሉትን ነጥቦች ከዚህ በታች እንመለከታለን።

የድሬዳዋ ታሪካዊ ድል

የጸሀይ መውጫው ክለብ በዚህ ዓመት ካካሄዳቸው አምስት ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን ብቻ በሜዳው አከናውኗል። ሜዳው ላይ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎችም አራት ነጥቦችን ማስመዝብ ችሏል። ሆኖም እስከ አምስተኛው ሳምንት ድረስ የድል ጸሀይ አልወጣለት ብላ የቆየችበት ድሬዳዋ ከነማ በአምስተኛው ሳምንት የዓመቱን የመጀመሪያ ሙሉ ሶስት ነጥብ አግኝቷል።

ድሬዳዋ ከነማ በሳምንቱ ያካሄደውን ጨዋታ ሙሉ ሶስት ነጥብ ያግኝበት እንጂ ውጤቱን ግን እንዲሁ በቀላሉ አልነበረም ያሳካው። ወደ ድሬዳዋ ተጉዞ የተጫወተው የፕሪሚየር ሊጉ አዲስ ክለብ ሆሳዕና ሃድያ ባለሜዳውን ሁለት ለባዶ መምራት ችሎ ነበር። ነገር ግን ሁለት ጎል ባስቆጠረበት ፍጥነት ሁለት ተጫዋቾቹን ወደ መልበሻ ቤት በመላክ የቀይ ካርድ ሰለባ ስለሆኑበት ለተጋጣሚው ቡድን እጁን ለመስጠት ተገድዷል። በዚህም ምክንያት የመሰረት ማኒ ልጆች በሁለቱ ስመ ሞክሼዎች ፈቃዱ ወርቁ እና ፈቃዱ ታደሰ ሶስት ጎሎች ሶስት ለሁለት ማሸነፍ ችሏል። ይህ ድሉም በዓመቱ ያሳካው የመጀመሪያ ድሉ በመሆኑ ታሪካዊ ሆኖ ተመዝግቦለታል። ውጤቱን ተከትሎም ከኮረንቲዎቹ እና ከሆሳዕና ሀድያ በላይ መቀመጥ ችሏል።

የፈረሰኞቹ ሀትሪክ

ቅዱስ ጊዮርጊስ በአምስተኛው ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ከዘወትር ተቀናቃኙ ኢትዮጵያ ቡና ጋር ተጫውቶ ባዶ ለባዶ መለያየት ችሏል። ይህ ውጤቱም ክለቡን በሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች መረቡን በጎል ሳያስደፍር የወጣበት ጨዋታ ሆኗል። በፈረሰኞቹ መረብ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ኳስ ማሳረፍ የቻለው የቀድሞ ተጫዋቻቸው የሲዳማ ቡናው አንዷለም ንጉሴ አቤጋ ሲሆን ይህም በሊጉ ሁለተኛ ሳምንት ነበር። ከሁለተኛው ሳምንት መርሃ ግብር በኋላ የተካሄዱትን ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች አንድ ለባዶ ማሸነፍ የቻለው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአምስተኛው ሳምንት ደግሞ ጎል ማስቆጠር ቢሳነው እንኳ መረቡን አስከብሮ መውጣት በመቻሉ ነው ሃትሪክ የሰራው።

የአቻነት ሳምንት

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከተካሄዱ ሰባት ጨዋታዎች አራቱ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁበት ሳምንት ይሄው አምስተኛው ሳምንት መርሃ ግብር ነው። ተመልካች ጎል እንዳማረው ያሳለፈበት ይህ ሳምንት ሶስት ጨዋታዎች ባዶ ለባዶ ተጠናቀውበታል። ይህም ማለት በአቻ ውጤት ጨዋታቸውን ካጠናቀቁት ስድስት ክለቦች በተጨማሪ አንድ ለባዶ የተሸነፉትን ወላይታ ድቻን እና አርባ ምንጭ ከነማን በመጨመር በአጠቃላይ ስምንት ክለቦች በዚህ ሳመንት ጎል ማስቆጠር አልቻሉም። ከ14 ክለቦች ስምንቱ ጎል ያላስቆጠሩበትን አምስተኛውን ሳምንት ስድስት ክለቦች ብቻ ናቸው ጎል ማስቆጠር የቻሉት። በዚህ ሳምንት በአጠቃላይ የተቆጠሩት ጎሎች ብዛትም 11 ብቻ ናቸው። ድሬዳዋ ከነማ በሶስት ጎሎች የሳምንቱ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሲሆን ከድሬዳዋ ቀጥሎ ያለውን ደረጃ ደግሞ ደደቢት፣ ሆሳዕና ሀድያ እና ኤሌክትሪክ በእኩል ሁለት ጎሎች ይከተላሉ። ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከነማ ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ጎል አስቆጥረዋል።

አራት ነጥብ ለደቡብ

በዚህ ሳምንት የደቡብ ክልል ክለቦች ድል ፊቷን አዙራባቸዋለች። ከአምስቱ የክልሉ ክለቦች መካከል ሲዳማ ቡና ብቻ ሙሉ ሶስት ነጥብ ሲያገኝ ሀዋሳ ከነማ ደግሞ አንድ ነጥብ አግኝቷል። ቀሪዎቹ የክልሉ ክለቦች ግን እጃቸውን ለሽንፈት ሰጥተው በባዶ ተመልሰዋል። ሆሳዕና ሀድያ በድሬዳዋ ሶስት ለሁለት እና አርባ ምንጭ ከነማ ደግሞ በሜዳው በአዳማ ከነማ አንድ ለባዶ ተሸንፈዋል። በአጠቃላይ በሳምንቱ የክልሉ ክለቦች በጎል በኩልም ማስቆጠር የቻሉት ሶስት ብቻ ነው ሲዳማ ቡና አንድ ሆሳዕና ሃድያ ሁለት።ቀሪዎቹ የጎሉን መስመር ማግኘት አልቻሉም

ያላሸነፉትና ያልተሸነፉት የሸገር ክለቦች

በዚህ ሳምንት ከተከሰቱት አዳዲስ ክስተቶች መካከል ስድስቱም የአዲስ አበባ ክለቦች ተጋጣሚወቻቸውን ማሸነፍ አለመቻላቸው ነው። መከላከያ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሜዳቸው በመውጣት ወደ ጎንደር እና ሀዋሳ ተጉዘው ያከናወኗቸውን ጨዋታዎች ያለ ግብ በአቻ ውጤት ማጠናቀቅ ሲችሉ ሰኞ አመሻሽ ላይ የተካሄደው የደደቢት እና ኤሌክትሪክ ጨዋታም ሁለት እኩል በሆነ ውጤት ነው የተጠናቀቀው። በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታም ያለምንም ግብ የተጠናቀቀ ጨዋታ ነው።

ከነጥብ በተጨማሪም ስድስቱም የአዲስ አበባ ከተማ ክለቦች በጋራ ማስቆጠር የቻሉት አራት ጎሎችን ብቻ ሲሆን እነሱንም ጎሎች ያስቆጠሩት ደደቢት እና ኤሌክትሪክ ናቸው። የደደቢትን ሁለት ጎሎች ያስቆጠረው ሳሙኤል ሳኑሜ ብቻውን ሲሆን እነዚህ ጎሎችም ተጫዋቹን በአምስት ጨዋታዎች ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ወደ አምስት ከፍ ያደረጉለት ሆነዋል።


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Mohammed Ali [720 days ago.]
 Xenkru allah kenante gar yihun siru ashenifacw yawancha baletbet tihonalchw keWOLAITA SODDO bodditi

Mohammed Ali [720 days ago.]
 Xenkru allah kenante gar yihun siru ashenifacw yawancha baletbet tihonalchw keWOLAITA SODDO bodditi

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!