የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ታሪክ
ታህሳስ 17, 2008

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ታሪክ

ክፍል አራት  

በይርጋ አበበ

እግር ኳስ ከጦርነቱ በፊት

ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ታሪክን በሚዳስሰው ዝግጅታችን የፌዴሬሽኑን 25ኛ ዓመት የብር ዕዮቤልዮ በዓል በማስመልከት የተዘጋጀውን ልዩ ዕትም መጽሔት የጻፉትን የአቶ ገዳሙ አብርሃን እና የክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማን ቃለ ምልልስ ማስነበባችን ይታወሳል። በዚያው ዝግጅታችንም እግር ኳስ ከጠላት ወረራ በፊት የነበረውን ገጽታ ታላቁ ኢትዮጵያዊ የእግር ኳስ ሰው አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ለሚጠይቋቸው ለአቶ ገዳሙ ከማስታወሻቸው እየገለበጡ ሲነግሯቸው አንብበናል። በዛሬው ዝግጅታችን ደግሞ ካለፈው የቀጠለውን ክፍል እንዲህ አሰናድተን አቅርበነዋል አብራችሁን ሁኑ።

እግር ኳስ በፋሽስት ዘመን

አቶ ገዳሚ አበራ ፋሽስት አገራችንን ይዞ በነበረበት ዘመን እግር ኳስ ምን አይነት መልክ እንደነበረው ለማወቅ አሁንም የክቡር ይድነቃቸው ተሰማን በር ለማንኳኳት ተገድደዋል። ሁለቱ ግለሰቦች በወቅቱ ስለነበረው የእግር ኳስ ሁኔታ ያደረጉትን ቃለ ምልልስ እንዲህ እንዘግበዋለን።

ጥያቄ፦ በወቅቱ የነበረውን የእግር ኳስ ሁኔታ ያስታውሱን

መልስ፦ እንደምታውቀው በኢጣሊያን ጊዜ የነበረው ሁኔታ ቀጥታ በዘር ልዩነት ነበር። በ፲፱፻፴ ዓ.ም ገደማ ኢጣሊያኖች ለአገሬው ህዝብ በወሰኑት ቀበሌ ማለትም አሁን የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ባለበት ስፍራ አንድ ያገር ተወላጅ የስፖርት ጽ/ቤት የሚል ድርጅት አቋቋሙና በብስክሌትም በእግር ኳስም በተለየ መንገድ በተለየ ሜዳ ከነጮች ሳንቀላቀል እርስ በእርሳችን ብቻ ስፖርትን እንድናዘወትር ተደረገ። በአስመራም በዚሁ መልክ ልዩ ልዩ ቡድኖች አቋቁመው አርዲታ፣ ሳቮያ፣ የሚሉ ስሞች እየተሰጣቸው ይጫወቱ ነበር። በአዲስ አበባም የጊዮርጊስን ቡድን ሊቶሪዮ ውቤ ሰፈር እንዲባል ሲደረግ የቀበናው ቪላ የኢጣሊያ የስድስት ኪሎው ፒያሳ ሮማ የጉለሌው ኮንሰላታ ተብለው እንዲጠሩ ተደረገ።

የአቶ ይድነቃቸው ማብራሪያ ይቀጥላል። ለጊዜው እዚህ ላይ ገታ እናድርገውና ከአቶ ይድነቃቸው መልሶች ላይ የተወሰኑ ነጥቦችን አንስተን እናብራራ።

ፋሽስት አገራችንን በተቆጣጠረበት ዘመን ያካሄደው የመጀመሪያ ስራ የአገሪቱን ነባር ታሪኮች ወደ ማጥፋቱ ነበር። ለዚህ እርምጃው ስኬትም የተቋማቱን ስያሜ በመቀየር የአገራቸውን ስያሜ መስጠት፣ የቀደሙ ተቋማትን ማፍረስ እና ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ አዲስ ተቋማትን ማቋቋም እና በኢትዮጵያዊያን ማህበረሰብ የነበረውን ህብረት በማጥፋት እንዳይቀራረቡ ማድረግ እንደነበረ ይህ የአቶ ይድነቃቸው ታሪካዊ ማስታወሻ ያመለክታል። በዚህ የፋሽስት እኩይ ተግባር ሰለባ ከሆኑት ገር በቀል ድርጅቶች እና ነባር ባህሎች መካከል ዘንድሮ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ አንዱ ነው። ጊዮርጊስ በፋሽስት ጊዜ ኢትዮጵያዊ ስያሜውን ጥሎ ጣሊያናዊ ስያሜ እንዲያንጠለጥል ተደርጎ እንደነበር አይተናል። ወደ አቶ ይድነቃቸው ታሪካዊ ማስታወሻ እንመለስ።

“የስፖርት ጽሕፈት ቤቱ አቋሙ ፖለቲካዊ መልክ ያዘለ ስለነበረ አዳዲስ የሚቋቋሙትን ቡድኖች የሀይማኖትና የጎሳ ስም እንዲይዙ ትዕዛዝ ይሰጥ ነበር። ይኸውም ከፋፍለህ ግዛ የተባለውን የፖለቲካ መመሪያ በመከተል ነበር። ከኳስ ተጫዋቾች መካከል እኔ ራሴ በስፖርት ጽ/ቤት ውስጥ እንድሰራ ስለተወሰነ የስፖርቱንና የውድድሮቹን ደንቦች ባማርኛ ስተረጉም በጉዳዩ ላይ የተጠናቀቀ ችሎታ ለማግኘት ቢረዳኝም በአንድ በኩል ደግሞ ምንም እንኳን የ፩፮ ዓመት ልጅ ብሆን የስፖርቱ ሞራላዊ መልክ እንዳልታሰበበት ለመገንዘብ አላዳገተኝም።

የስፖርቱ ሞራላዊ መልክ አልተጠበቀም ለማለት ካበቁኝ ምክንያቶች አንዱ፦ አንድ ጊዜ የኢጣሊያኖች የሽዋ እና የኤርትራ ምርጥ ቡድኖች በሚጫወቱበት ቀን በ፰ ሰዓት ላይ የጊዮርጊስና የስድስት ኪሎ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ በነጮች ሜዳ እና በነጮች ተመልካች ፊት እንዲጫወቱ ተደርጎ የኳስ ጫማ ለነጮች ብቻ የተፈቀደ በመሆኑ የምንጫወተው ጥቂቶች ተጫዋቾች ባዶ እግራችንን እንድንጫወት ከመገደዳችንም በቀር እርስ በእርሳችን በምንጋጭበት ጊዜ ሁሉ አጫዋቹ ዳኛ እየሳቀ ከመመልከት በቀር አንድም ቅጣት ወይም ግሳጼ አይሰጥም ነበር። ተመልካቹም ህዝብ ከጨዋታው ይልቅ ድብድቡ ይጥመው ለነበር በማጨብጨብና በመሳቅ በጠቡ እንድንገፋበት ስላደረገን እርስ በእርሳችን ተፋጅተን ጨዋታውም ሳይፈጸም ተቋርጦ ተጫዋቾችንም ተመልካቾች እንደ ሰርከስ ተጫዋቾች አስቀን ከሜዳ ወጥተናል።

ጊዜ አልፎ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ደንቦች ለማዘጋጀት እድል በገጠመን ጊዜ የዚህ አይነቱ አሳዛኝ ሁኔታ ለወደፊቱ እርምጃችን ትምህርት ስለሰጠን ማስጠንቀቂያነቱ ጠቅሞናል። ከ፲፱፻፴ እስከ ፲፱፻፴፫ ባለው ጊዜ ውስጥ ይኸው ላገር ተወላጅ ጽ/ቤት ተብሎ የተቋቋመው ጽ/ቤት በዚያው ባዲሱ ከተማ አካባቢ ብቻ በኢትዮጵያኖች መካከል ውድድር እንዲያደርግ ይፈቀድ ነበር።

ማን ያውራ የነበረ ማርዳ የቀበረ ነውና ብሒሉ በወቅቱ ኖረው ሂደቱን በጥልቀት የተከታተሉት ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማም በክቡር ማስታወሻቸው ያሰፈሩልንን ታሪክ ከዚህ በላይ አይተናል። በወቅቱ ቅኝ ገዥው የቤኒቶ ሞሶሎኒ አሽከር ጄኔራል ግራዚያኒም በሌሎች አገሮች ቅኝ ገዥዎች በሚገዟቸው አገራት የሚኖሩ ህዝቦችን የግፍ ጽዋ እንደሚያደርሱባቸው ሁሉ እሱም በእኛ ላይ ተመሳሳዩን ግፍ ፈጽሞብን እንደነበረ ይህ ታሪክ ምስክር ነው። የአውሮፓዊያን ቅኝ ገዥዎች ወረራ በሚያካሂዱበት ጊዜ የሚገዙትን አገር ህዝብ በቀላሉ ለማንበርከት ከሚጠቀሙባቸው ስልቶች መካከል አንዱ እና ምናልባትመ ውጤታማ ሆኖ የተገኘው በአገሬው መካከል መከፋፈልን መዝራት ነበር። ይህ አካሄዳቸውንም ከፋፍለህ ግዛ ወይም Divine Rule ሲሉ ይጠሩታል። ኢትዮጵያን ለአምስት ዓመታት የገዛው ፋሽስትም የግዛት ዘመኑን ለማስረዘም የተጠቀመው ይህኑ የከፋፍለህ ግዛ ሰይጣናዊ ፍልስፍናውን ሲሆን ይህን ፍልስፍናውንም በእግር ኳስ ሜዳ ሳይቀር ሲተገብረው እንደነበረ አቶ ይድነቃቸው ሲናገሩ እንመለከታለን።

እግር ኳስ ከማንኛውም ልዩነት ማለትም የዘር የሀይማኖት የፖለቲካ የአመለካከት ነጻ የሆነ ስፖርት ቢሆንም ፋሽስቶች ግን በኢትዮጵያዊያን መካከል አንድነት እና ህብረት እንዳይኖር ስታዲየሞች ሁሉ በዘር የተመሰረተ ፓርላማ አድርገውት አረፉ። ይህ የፋሽስቶች ደባ ግን አሁንም ድረስ በርካታ የአገራችን ክለቦች በብሔራቸውና በጎጣቸው እየተጠሩ መሆኑን ስንመለከት አንድም የፋሽስቶች ጥላ እየተከተለን ነው ወዲህ ደግሞ ስልጣኔ ስላልገባን አሁንም በድሮ በሬ እያረስን የምንገኝ ህዝብ ሆነናል ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል።

ይቀጥላል!!!


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!