የሰባተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ቅኝት
ታህሳስ 22, 2008

ሰባቱም ጨዋታዎች በመሸናነፍ ተጠናቀዋል  

ታፈሰ ተስፋዬ 123ኛ የፕሪሚየር ሊግ ጎሉን አስቆጥሯል

በይርጋ አበበ

ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ 45 ቀናት የሚቋረጠው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ትናንት ከቀትር በኋላ እና አመሻሹ ላይ በተካሄዱ ሰባት ጨዋታዎች ተካሂዶበታል። ስድስቱ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰዓት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ የተካሄዱ ሲሆን ሁሉም ጨዋታዎች የተከናወኑት ከአዲስ አበባ ውጭ ነበር። አንዱ ጨዋታ ብቻ በአዲስ አበባ ስታዲየም የተካሄደ ሲሆን እሱም የሳምነቱ ታላቅ ጨዋታ የሚል ስያሜ የተሰጠው የደደቢትና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ነው። ጨዋታዎቹ ምን መልክ ነበራቸው? እነማን ተሳካላቸው ያልተሳካላቸውስ የትኞቹ ናቸው?የሚሉትን ጥያቄዎች ከዚህ በታች ያለው ሀተታ በሚገባ መልስ ይሰጥበታል።

ከሽንፈት ሀንጎበሩ መውጣት ያልቻለው ቡና

ኢትዮጵያ ቡና ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ወደ ክልል ተጉዞ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማምጣት የጠፈር ያህለ እየራቀው መጥቷል። ትናንትም ወደ አርባ ምንጭ ተጉዞ ሁለት ለባዶ ተሸንፎ ተመልሷል። በስድስተኛው ሳምንት መርሃ ግብር በአወዛጋቢ የዳኛ ውሳኔ እና በግብ ጠባቂው ግዙፍ ስህተት በደደቢት የተሸነፈው የድራጋን ፖፓዲች ቡድን ትናንትም አርባ ምንጭ ላይ ለባለሜዳው አርባ ምንጭ ከነማ እጁን ለመስጠት ተገድዷል። ቡና በተለይ በተከላካይ መሰመሩ በኩል ክፍተት እንደነበረበት የገለጹት የኢትዮፉትቦል ዶትኮም ምንጮች የተለመደው የግብ ጠባቂው ድክመንት አልተቀረፈም ነበር ብለዋል። በዚህም አርባ ምንጭ ከነማ በሜዳው ሙሉ ሶስት ነጥብ በማግኘት ባለፈው ሰኞ በኤሌክትሪክ የደረሰበትን የሁለት ለባዶ ሽንፈት ማወራረድ አስችሎታል። ቡና ደግሞ በድጋሚ ተሸንፏል።

የዓመቱን የመጀመሪያ ድል ያገኘው ሆሳዕና ሀድያ

ሆሳዕና ሀድያ በዚህ ዓመት ስድስት ጊዜ ተጫውቶ በአምስቱ የሽንፈት ጽዋን በሚገባ ያጣጣመ እና አንድ ጊዜ ብቻ አቻ በመውጣት አንድ ነጥብ ይዞ የደራው ግርጌ ላይ ተረጋግቶ የነበረ ክለብ ነው። በሰባተኛው ሳምንት መርሃ ግብር ግን በሜዳው የጋበዘውን ጎረቤቱን ወላይታ ድቻን አምስት ለባዶ በማሸነፍ እሱም ማሸነፍ እንደሚችል አሳይቷል። አምስት የተለያዩ ተጫዋቾች የሆሳዕናን ጎሎች ያስቆጠሩ ሲሆን ለወላይታ ድቻ ከማስተዛዘኛነት ያልዘለለች ጎል ያስቆጠረው ደግሞ ባለፈው የውድድር ዓመት ለሆሳዕና ከነማ ይጫወት የነበረው ቴዎድሮስ መንገሻ ነው ያስቆጠረው።

ሁለቱ የደቡብ ክልል ክለቦች ውጤት ፊቱን የዞረባቸው ሲሆን ወላይታ ድቻ ያለፉትን ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች በመሸነፍ የውጤት መንሸራተት ውስጥ ሲገኝ ትናንት የዓመቱን የመጀመሪያ ድሉን የተቋደሰው ሆሳዕና ሀድያ በበኩሉ በአጠቃላይ አራት ነጥቦችን ብቻ በመሰብሰብ 14ኛ ላይ ብቻውን ተቀምጦበታል።

የመሰረት ማኒ ሀትሪክ

መሰረት ማኒ የትውልድ ከተማዋን ክለብ እየመራች ወደ ፕሪሚየር ሊግ ካደገች በኋላ ያካሄደቻቸውን አራት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ ተስኗት ቆይታ ነበር። ሆኖም ግን የትናንቱን ጨምሮ በአጠቃላይ በሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፍ ቡድኗ ሃትሪክ ሰርቷል። ትናንትናም በድሬዳዋ ስታዲየም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን አስተናግዶ አንደ ለባዶ በማሸነፍ የነጥብ ድምሩን አስር በማድረስ ከንግድ ባንክ፣ መከላከያ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ዳሽን ቢራ እና ሀዋሳ ከነማ በላይ በመሆን አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።   

ያልተኘነፈው አዳማ ከነማ እና የታፈሰ ተስፋዬ ክብረ ወሰን

ስድስት ጨዋታዎች በማሸነፍ በአንድ ጨዋታ ብቻ አቻ ወጥቶ የነጥብ ድምሩን 19 አድርሷል አዳማ ከነማ። ክለቡ ስድስት ጨዋታዎች ሲያሸንፍ አጥቂው ታፈሰ ተስፋዬ በበኩሉ ስድስት ጎሎችን በማስቆጠር በፕሪሚየር ሊጉ የከፍተኛ ጎል አግቢነት ደረጃውን ከሳሙኤል ሳኑሚ በአንድ በልጦ መምራት ችሏል። በአጠቃላይ በአራት ክለቦች ማሊያ ያስቆጠራቸውን የፕሪሚየር ሊግ ጎሎች ብዛትም 12 በማድረስ የምንጊዜም የፕሪሚየር ሊጉ ከፍተኛ ጎል አግቢ ሆኗል። በሜዳው አዳማ ከነማን አስተናግዶ ሁለት ለአንድ የተሸነፈው የውበቱ አባተ ቡድን ሀዋሳ ከነማ በበኩሉ በተከታታይ ሶስት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ተስኖት በስድስት ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ከሆሳዕና ሃድያ ጋር ተጎራብቷል። አራት የጎል እዳም ተሸክሟል። በፕሪሚየር ሊጉ በርካታ የጎል እዳ ያለበት ክለብ ሀዋሳ ከነማ ሲሆን ጎረቤቱ ወላይታ ድቻም በተመሳሳይ አራት ጎል እዳ አለበት። የወራጅ ቀጠናውን በብቸኝነት የተቆጣጠረው ሆሳዕና ሀድያ ከሁለቱ ነባር የሊጉ ክለቦች በተሻለ ሁለት የጎል እዳ ብቻ ነው ያለው።

 ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ዳሽን

ዳሽን ቢራ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን ካሸነፈ በኋላ ያሉትን ቀሪ ሶስት ጨዋታዎች ማሸነፍ ተስኖት ቆይቶ ነበር። ትናንት ግን በሜዳው ፋሲለደስ ስታዲየም ኮረንቲውን አስተናግዶ በባዶ ሸኝቶታል። ዳሽንን ወደ አኘሸናፊነት የመለሰችዋን ብቸኛ ጎል ኮረንቲው መረብ ላይ ያሳረፈው ሸሪፍ ዲን ነው። ዳሽን ማሸነፉን ተከትሎ ነጥቡን አስር በማድረስ ደረጃውን ወደ ስድስት ማሳደግ ችሏል። ባለፈው ሳምንት አርባ ምንጭ ከነማን ሁለት ለባዶ ያሸነፈው ኤሌክትሪክ በበኩሉ ከሁለት የጎል እዳ ጋር ሰባት ነጥብ ይዞ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በሌላ የእለቱ ጨዋታ ወደ ይርጋለም የተጓዘው መከላከያ ተከላካዩ ቴዎድሮስ በቀለ በራሱ ግብ ላይ በማስቆጠሩ ለባለሜዳው ሲዳማ ቡና ሙሉ ሶስት ነጥብ አስረክቦ ተመልሷል። መከላከያ ደረጃውን ወደ ስምንተኛ ዝቅ ሲያደርግ አሸናፊው ሲዳማ ቡና በበኩሉ ሶስተኝነትን ተቆናጦታል።

  በተከታታይ መረቡን ያላስደፈረው ኦዶንካራ እና የፈረሰኞቹ ተከታታይ ድል

ባሳለፍነው ሳምንት የተካሄደውን ስድስተኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ኢንተርናሽናል አልቢትር ለሚ ንጉሴ የሰሩትን ስህተት ተጠቅመው ኢትዮጵያ ቡናን ሁለት ለአንድ ያሸነፉት ሰማያዊ ለባሾቹ ደደቢቶች ትናንት ምሽት ግን ለፈረሰኞቹ በቀላሉ እጃቸውን ሰጥተዋል። 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓላቸውን እያከበሩ ያሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አዳነ ግርማ እና ብሪያን አሙኒ ባስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች ሁለት ለባዶ ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን ይህ ውጤታቸውም በአምስት ተከታታይ ጨዋታ መረባቸውን ሳያስደፍሩ የወጡበት ጨዋታ ሆኗል።

ሙሉ የጨዋታ ብልጫ እና የጎል ሙሉ የጨዋታ ብልጫ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ የጎሉን ብዛት ከዚህም በላይ የሚጨምርበት እድል ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም አጥቂዎቹ የተጋጣሚያቸውን መረብ ጠንቅቀው ማየት ባለመቻላቸው በቀላሉ አምክነዋቸዋል። ውጤቱን ተከትሎም ደደቢት ከነበረበት ሶስተኛ ደረጃ ወደ ታች አንደ ወርዶ አራተኛ ደረጃን ሲይዝ ፈረሰኞቹ ከመሪው አዳማ ከነማ በሶስት ነጥብ ተበልጠው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ሰባተኛው ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ከዚህ በላይ ባለው መልኩ የተጠናቀቀ ሲሆን ከሰባት ሳምንታት በኋላ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
biss [715 days ago.]
 @ethiofootball.....በአጠቃላይ በአራት ክለቦች ማሊያ ያስቆጠራቸውን የፕሪሚየር ሊግ ጎሎች ብዛትም 12 በማድረስ የምንጊዜም የፕሪሚየር ሊጉ ከፍተኛ ጎል አግቢ ሆኗል።...needs editing 12 goals...??

ABEL [709 days ago.]
 SAWNT LAMN SPORT AKAM

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!