ሐዋሳ ከነማ አምስት ተጫዋቾቹን ሊያሰናብት ነው
ታህሳስ 25, 2008


በይርጋ አበበ

ውጤት ፊቷን ያዞረችበት ሀዋሳ ከነማ ለውጤቱ መጽፋት የተጫዋቾች ጉዳት እና የአቋም መውረድ መሆኑን አስታወቀ። ከክለቡ የውስጥ ምንጮች ካገኘነው መረጃ ለማወቅ እንደተቻለው በአሁኑ ወቅት በተለይ በተከላካይ እና አጥቂ ክፍሉ ላይ ከፍተኛ ክፍተት እየታየበት በመሆኑ ለተደጋጋሚ ሽንፈቱ ተጠያቂ የሆኑ ተጫዋቾች ከክለቡ እንዲሰናበቱ ሳይወስን አልቀረም።

በተለይ ተደጋጋሚ ስህተት የሚሰራው የተከላካይ ክፍሉ አባል የሆነው አዲስዓለም ተስፋዬ አንዱ ሲሆን ተጫዋቹ ብቃቱን እንዲያሻሽል እድል እንዲሰጠው ሀሳብ ቀርቦለታል። ባለፈው ዓመት ከአርባምንጭ ከነማ በ900 ሺህ ብር ክለቡን የተቀላቀለው አጥቂው ገብረሚካኤል ያዕቆብ ከክለቡ እንዲለቅ ተነግሮታል ተብሏል። ተጫዋቹ ክለቡን ከተቀላቀለበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት ሁለት ዓመታት አንድ ጎል ብቻ ማስቆጠሩን ተከትሎ ከደጋፊውና ከክለቡ አመራሮች ጫና እየደረሰበት መሆኑን ተከትሎ ተጫዋቹም የልቀቁኝ ጥያቄ ሳያቀርብ እንዳልቀረ ተነግሯል።

ከሁለቱ ተጫዋቾች በተጨማሪ ሌሎቹ አጥቂዎች ማለትም ከደደቢት በዚህ ዓመት ሀዋሳ ከነማን የተቀላቀለው በረከት ይሳቅ እና ባለፈው የውድድር ዓመት ከሰበታ ከነማ ሀዋሳ ከነማን የተቀላቀለው ሌላው አጥቂ አንተነህ ተሻገርም ከክለቡ እንዲለቁ የሚደረጉ ተጫዋቾች ናቸው። ሁለቱ አጥቂዎች በዚህ ዓመት ለክለቡ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከተጠበቀው በታች በመሆኑ ደጋፊውም ሆነ አመራሩ በተጫዋቾቹ ላይ እምነት አጥቶባቸዋል።

ጉዳት ላይ የሚገኘው የቀድሞው የደደቢት አጥቂ ግዙፉ ተመስገን ተክሌ በበኩሉ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ህክምናውን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እየተከታተለ ሲሆን ለተጨማሪ ህክምና ወደ ውጭ አገር ሂዶ እንዲታከም የተወሰነለት በመሆኑ ከሀዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብ የመልቀቂያ ደብዳቤ ተሰጥቶታል። ተጫዋቹ ከዓመታት በፊት ጀምሮ በደረሰበት ጉዳት በቂ ህክምና ባለማድረጉ በአሁኑ ሰዓት የእግሩ ጤንነት አስጊ መሆኑን ለተጫዋቹ ቅርብ የሆኑ የኢትዮፉትቦል ዶትኮም ምንጮች ገልጸውልናል። ሀዋሳ ከነማ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ካካሄዳቸው ሰባት ጨዋታዎች ስድስት ነጥቦችን ብቻ በመሰብሰብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!