የፈረሰኞቹ 80ኛ ዓመት በሲምፖዚየም ሲዘከር
ጥቅምት 25, 2008

በይርጋ አበበ

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ይገኛል። ክለቡ ከታህሳስ 9 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2008 ዓ.ም በሚያከብረው የበዓሉ ክብረ ዝግጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የሲምፖዚየም ዝግጅት ትናንት በሸራተን አዲስ ሆቴል ተካሂዷል። ታዋቂው ጋዜጠኛ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ “የፒያሳ ልጅ” የሚለው መጽሃፍ ደራሲ የሆኑት አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ የዝግጅቱን መድረክ የመሩ ሲሆን ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የክለቡ የቀድሞ ተጫዋቾች በዝግጅቱ ታዳሚ ሆነዋል። በእለቱ ከተካሄዱ የዝግጅቱ ክፍሎች እና ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ለአንባቢያን ይበጃሉ ያልናቸውን ዘግነን አቅርበናቸዋል።

ስለማዘውተሪያ ስፍራ ችግር

በእለቱ የክብር እንግዶች የመክፈቻ ንግግር ካቀረቡ በኋላ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ለኢትዮጵያ ስፖርት ያበረከተውን አስተዋጽኦ አቶ ወንዱ ለገሰ ካቀረቡ በኋላ ጥሪ የተደረገላቸው የክለቡ ሰዎች አስተያየትና ጥያቄ አቅርበዋል። በእለቱ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል “የኢትዮጵያ እግር ኳስ ወርቃማ ዘመን” የሚል ሀረግ እየጠቀሱ አስተያየት የሰጡ ጠያቂዎች “ነገር ግን በዚህ ዘመን የአገራችን እግር ኳስ ምንም ማታለል ሳያስፈልገን ወደ ኋላ ተንሸራቷል። እድገቱ የኋሊት የሆነውም የታዳጊዎች የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ ስለሌለ ነው። ይህንን በተመለከተ በተለይ መንግስት ምን እቅድ አለው?” የሚሉ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ተነስተው ነበር። ከረፋዱ አራት ሰዓት ገደማ በተጀመረው ሲምፖዚየም ላይ የተገኙት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴን እነዚህ ጥያቄዎች በቀጥታ ይመለከቷቸው ስለነበረ ለጥያቄዎቹ መልስ ሰጥተዋል።

አቶ ሬድዋን የተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በትክክል ውሃ የሚቋጥሩ መሆናቸውን አምነው መንግስታቸውም ችግሩን ለመቅረፍ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናገሩ። በተለይ የታዳጊዎች የስፖርት ማዘውተሪያ ችግርን በተመለከተ ከፍተኛ ስራ መንግስታቸው እንደሚጠብቀው ገልጸው ነገር ግን ሌሎች ባለ ድርሻ አካላትም ለዚህ ጉዳይ ከፍተኛ ርብርብ እንዲያደርጉ ተማጽነዋል።

በዚህ የአቶ ሬድዋን መልስ ላይ ተጨማሪ አስተያየት የሰጡት ደግሞ አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ናቸው። አቶ ፍቅሩ “በእኛ ዘመን በባዶ እግራችን የምንጫወትባቸው በርካታ ሜዳዎች ነበሩ። የዛሬ ልጆች ግን ከአስፓልት ነጻ የሆነ ሜዳ የማያገኙ ከመሆኑም በላይ በኮንዶሚኒየም ቤቶች አካባቢ እንኳ ህጻናት የሚዝናኑበት ነጻ መሬት አይገኝም። በተለይ የኮንዶሚኒየም ግንባታዎችን ስመለከት የመሃንዲሶቹ እና ኢንጂነሮቹ አስተሳሰብ ይገርመኛል። መንግስትም ቢሆን ይህን ጉዳይ በሚገባ ሊመለከተው ይገባል” ሲሉ ነበር የተናገሩት።

አልኮል እና ስታዲየም

የአዲስ አበባ ስታዲየምን ዙሪያ ታክከው የተገነቡ ሱቆች የሚሰጡት አገልግሎት በብዛት የመጠጥ አገልግሎት ነው። የስታዲየሙ የላይኛው ክፍልም ቢሆን በብዛት የተሸፈነው በቢራ ማስታወቂያዎች ነው። ከዚህም በላይ ደግሞ አንዳንድ ክለቦች የቢራ ማስታወቂያ ይሰራሉ። አልኮል እና ስፖርት አብሮ ይሄዳል ወይ? ሲሉ አንድ ጠያቂ ጥያቄ አቅርበው ነበር። 

ለዚህ ጥያቄ መልስ የሰጡት አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ናቸው። አቶ ፍቅሩ ሲመልሱ “በአንደ በኩል ወጣቱን ኳስ ተጫወቱ እያልን በሌላ በኩል ደግሞ ቢራ ጠጡ ማለት አላስፈላጊ ስራ ነው። ነገር ግን በተለይ የእኛ እግር ኳስ ስላላደገ እና በኢኮኖሚም አገራችን ድሃ በመሆኗ ለእግር ኳስ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ የሚሆኑት የቢራ እና የትንባሆ ፋብሪካዎች ብቻ ናቸው። እኔ በዚህ ሰዓት አገሪቱ ውስጥ የቢራ ፋብሪካዎች ከክለብ እሰከ ብሔራዊ ቡድን ስፖንሰር ተደርገው ሳይ አዝናለሁ” ሲሉ መልሰዋል።

ይቀጥላል!!

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!