የፈረሰኞቹ ታላላቅ ሰዎች በሲምፖዚየሙ ከተናገሩት
ታህሳስ 30, 2016

በይርጋ አበበ

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በአፍሪካ ደግሞ ከቀዳሚዎቹ መካከል አንዱ የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት ክብረ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ መሆኑ ይታወቃል። ክለቡ በአሁኑ ወቅት በተለየ መልኩ በወንዶች እግር ኳስ ውጤት ላይ እና በሴቶች እግር ኳስ ደግሞ ተጫዋቾችን ከታች ጀምሮ በማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑ በስፋት የሚታወቅ ቢሆንም ከዚህ በተጓዳኝ ግን የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር በክብደት ማንሳት ቦክስ ቮሊ ቦል እና ሌሎች ስፖርቶችም ለአገሪቱ በርካታ ስፖርተኞችን ማፍራት ችሏል።

እኛም ዛሬ ትኩረት የምናደርገው በክለቡ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን ላይ ሲሆን በሲምፖዚየሙ ላይ ከተገኙት ተጋባዥ የክለቡ ሰዎች መካከልም አስተያየት የሰጡት የቀድሞ እና የአሁን ተጫዋቾች ናቸው። ከአነዚህ ተጫዋቾች መካከል በተለይ አሰልጣኝ አስራት ሀይሌ፣ ገብረ መድህን ሀይሌ፣ ሙሉዓለም ረጋሳ፣ ደጉ ደበበ እና የክለቡ ፕሬዚዳንት አብነት ገብረመስቀል የሰጡትን አስተያየቶች እናቀርባለን።

ደጉ ደበበ

ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ፈረሰኞቹን የተቀላቀለውና ስምንት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን ከፈረሰኞቹ ጋር ማንሳት የቻለው የቀድሞው የአርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ተጫዋች ደጉ ደበበ በአሁኑ ሰዓት የፈረሰኞቹ አምበል ነው። የክለቡን ጉዞ አስመልክቶ በተዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ ተገኝቶ አስተያየቱን የሰጠው የወቅቱ አምበል “ላለፉት 11 ዓመታት ከክለቡ ጋር ቆይታ አድርጌ ስምንት ዋንጫ አንስቻለሁ። ለዚህ ስኬት ያበቃን ምክንያቱ በክለቡ ውስጥ ያለን ሁላችንም ባለድርሻዎች ማለትም ተጫዋች አሰልጣኝ እና የክለብ አመራሮች መካከል ጠንካራ የአንድነት መሰረትና የስራ ባህል በመኖሩ ነው” ብሏል።

አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ

የቀድሞው የፈረሰኞቹ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ገብረመድህን በአሁኑ ሰዓት ከመከላከያ እግር ኳስ ክለብ ጋር ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሚያሳትፈውን ውጤት አስመዝግቧል። ገብረመድህን በፈረሰኞቹ ሲምፖዚየም ላይ ተገኝቶ ሀሳቡን ሲሰጥም “ክለቡ ለምን የራሱ ሜዳ እንዲኖረው አልተደረገም እኔ ተጫዋች በነበርኩበት ጊዜ እንደነበረው አሁንም የራሱ ሜዳ የለውም። ክለቡ በአገር ውስጥ ያለውን የበላይነትና ተጽእኖ ፈጣሪነት በተደጋጋሚ በኢንተርናሽናል ጨዋታ የመወዳደር እድል በመጠቀም በአህጉራዊ ደረጃ ሊደግመው ይገባል። ምክንያቱም ክለቡ ውጤት ሊቀይሩ የሚችሉ ተጫዋቾችን የመግዛት አቅም እንዳለው አቃለሁ” ያለ ሲሆን አያይዞም “ለክለባቸው ጥሩ ስራ የሰሩ ተጫዋቾች አብዛኞቹ በአሁኑ ሰዓት ኑሯቸው ጥሩ የሚባል ቢሆንም ከዚህ በተቃራኒው የሚገኙትን ክለቡ በባትሪም ቢሆን ፈልጎ በማግኘት ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል” በማለት ተናግሯል።

አስራት ኃይሌ

በዓሉ መከበሩን ያደነቀው በክለብ እና በብሔራዊ ቡድን ውጤታማው አሰልጣኝ አስራት ሀይሌ “ደርግ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚለው ስም እንዳይነሳበት በመፈለጉ ክለባችንን እንዲፈርስ ማድረጉ ይታወሳል። በዚያ ክፉ ወቅት የጊዮርጊስ ልጆች ትግል ፍሬ የሚባል ክለብ ሲቋቋም በዚያ ውስጥ ገብተን የጊዮርጊስ ምልክት እንዳይጠፋ የትግል ፍሬ ማሊያ የጊዮርጊስን እንዲመስል የክለቡን ኃላፊዎች ጠይቀን ስለተፈቀደልን የትግል ፍሬ ማሊያ ሙሉ በሙሉ የቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲመስል ስላደረግን የጊዮርጊስ ደጋፊዎች ከስታዲየም እንዳይጠፉ ማድረግ ችለናል” ሲል ተናግሯል። አስራት አያይዞም ያንን ገድል የሰሩ የክለቡ ተጫዋቾች ውለታቸው እምብዛም ሲወሳ እንደማይታይ ጠቅሶ ይህም ውለታን እንደመዘንጋት እንደሚቆጠር ተናግሯል።

ሙሉዓለም ረጋሳ

ጥበበኛው የመሃል ሜዳ አርክቴክት ሙሉዓለም ረጋሳ ከፈረሰኞቹ ጋር ስኬታማ ጊዜያትን ያሳለፈ ሲሆን ወደ ክለቡ ዋናው ቡድን ያደገበትን አጋጣሚ በማውሳት መናገር ጀምሯል። ሙሉዓለም ሲናገር “በርካታ ተጫዋቾች በጠፉበት 1989 ዓ.ም ለክለቡ ሲ ቡድን የምጫወት ቢሆንመ አስራት ኃይሌ ግን ይህን ልጅ እቀይረዋለሁ ብሎ ወደ ዋናው ቡድን ካሳደገኝ በኋላ በጊዜ ከወሳኝ ተጫዋቾች መካከል አንዱ እንድሆን አድርጎኛል” ያለ ሲሆን ለዚህም ክለቡ ተጫዋቾችን በማሰደግም ሆነ በታዳጊዎች ላይ እምነት የሚጥል አሰልጣኝ ባለቤት መሆኑን ጠቅሷል።

ሙሉዓለም አያይዞም “ቅዱስ ጊዮርጊስ የተጫዋቾችን ማንነት ከመቅረጽ ጀምሮ በኑሯቸው የተሻሻሉ እንዲሆኑ ድጋፍ ያደርጋል። ለተጫዋቾች የፊርማ ገንዘብ ለመጀመሪያ ጊዜ መክፈል የጀመረው ጊዮርጊስ ነው። ይህም በኑሯችን ላይ አስፈላጊ የሆኑ ጥቅማጥቅሞችን እንድናገኝ ያደረገ ከመሆኑም በላይ ሀላፊነት እንዲሰማን በማድረግ አሳድጎናል” ሲል ተናግሮ አሁንም ይህ ባህሉ እንደቀጠለ መሆኑን አውስቷል።

አቶ አብነት ገብረመስቀል

የክለቡ ፕሬዚዳንት ከአባታቸው እና ከአጎታቸው ጀምሮ የተሳሰረ የክለቡ ፍቅር እንዳላቸው ይናገራሉ። አቶ አብነት የክለቡን ቀጣይ ጉዞ የሚዳስስ ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በተለይም በክለቡ የምስረታ በዓል ከጠንካራዎቹ የደቡብ አፍሪካ እና ምዕራብ አፍሪካ ወይም ሰሜን አፍሪካ ክለቦች ከመጋበዝ ይልቅ ለምን የኬኒያ ክለብ ጋበዛችሁ? ለሚለው የኢትዮፉትቦል ዶትኮም ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል። ክለቡ የምስረታ በዓሉን ለማክበር ሲዘጋጅ በቅድሚያ የወዳጅነት ጨዋታ ሲያስብ ጥሪ ያቀረበው ለግብጹ አል አህሊ እና ለሱዳኑ ኤል ሜሪክ እንደነበረ ገልጸው ነገር ግን የግብጹ አል አህሊ በ18 ቀናት ውስጥ ሶስት የሊግ ውድድር ስላለበት ዋናውን ቡድን መላክ እንደማይችል ነገር ግን ሁለተኛውን ቡድን ልላክላችሁ ብሎ ሲነግራቸው ፊታቸውን ወደ ኬኒያው ቡድን ማዞራቸውን ተናግረዋል። “ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ወይም ካፍ ለበዓላችን ማድመቂያ በቻምፒዮንስ ሊጉ ማጣሪያ ከዴሞክራቲክ ኮንጎው ቴፒ ማዘምቤ ጋር መደልደሉ አንዱ የበዓላችን ማድመቂያ ሆኖልናል” ብለዋል።


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!