የታሰበለትን ግብ መምታት ያልቻለው የወዳጅነት ጨዋታ እና የቻን ቡድን ታክቲካል ዳሰሳ
ጥር 02, 2008

በይርጋ አበበ

ከትናንት በስቲያ አመሻሹ ላይ ዋልያዎቹ በሜዳቸው አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ከኒጀር አቻቸው ጋር ያደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ ግቡን የመታ እንዳልነበረ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን ጨምሮ በስታዲየም የተገኙ ተመልካቾችም ተናግረዋል። ጨዋታው የተዘጋጀው ሁለቱ አገሮች ከሳምንታት በኋላ በሩዋንዳ ለሚካሄደው አራተኛው የቻን ዋንጫ ውድድር ላይ ቡድናቸውን እንዲፈትሹ ቢሆንም በተለይ የኒጀር ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በሜዳ ላይ ዲስፕሊን አመለ ብልሹዎች በመሆናቸው ጨዋታው የተጠበቀውን አገልግሎት ሳይሰጥ መጠናቀቁ በርካቶችን አስገርሟል።

ከጨዋታው በኋላ ለጋዜጠኞች አስተያየታቸውን የሰጡት የዋልያዎቹ አለቃ ዮሐንስ ሳህሌ “ጨዋታው እንዳሰብነው አልሆነልንም ምክንያቱም በእነሱ በኩል ፋኦሎች ተደጋግመው ይሰሩ ነበር። የወዳጅነት ጨዋታ ቢሆንም ከልጆቼ ማየት የምፈልገውን ነገር ማየት እንዳልችል አድርጎኛል” ያሉ ሲሆን በቀጣይ አንድ የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚካሄድ ገጸው በዚያ ጨዋታ እና በትናንቱ ጨዋታ የተመለከቷቸውን የተጫዋቾቻቸውን ክህሎት በማየት በውድድሩ ቋሚ ተሰላፊዎቻቸውን እንደሚለዩ ገልጸዋል። ከአንዳንደ መረጃዎች ለማወቅ እንደሞከርነው ብሔራዊ ቡድኑ የወዳጅነት ጨዋታ የሚያካሂደው ከግብጽ ብሔራዊ ቡድነ ጋር ሲሆን ጨዋታው የሚካሄደውም ነገ አመሻሹ ላይ ይሆናል።

አንዳንድ ነጥቦች ስለ ትናንቱ ጨዋታ ታክቲካዊ ትንታኔዎች

የአማካይ ተከላካዩ ተስፋዬ አለባቸው ሚና

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ስብስባቸው የጠሯቸውን እንደ ተስፋዬ አለባቸው፣ ታፈሰ ተስፋዬ እና ታደለ መንገሻ ያሉ ተጫዋቾችን ያሰለፉ ሲሆን ሙሉዓለም ጥላሁንም ለመጀመሪያ ጊዜ የመጫወት እድል ተሰጥቶታል። በተለይ የፈረሰኞቹ አማካይ ተከላካይ ተስፋዬ አለባቸው የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት የሚችል መሆኑን ያመላከተ ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴ ያሳየ ሲሆን የተከላካይ ክፍሉን በሚገባ በማገዝ በኩል የነበረው ቁርጠኝነት ከፍተኛ ሆኖ ታይቷል።

አማካይ ተከላካዩ ካለው ተፈጥሯዊ የተከላካይነት ልምድ አኳያ በተለይ በእለቱ በራስ መተማመኑ ዝቅተኛ ሆኖ የታየውን የዳሽን ቢራውን ያሬድ ባየህን ሽፋን በመስጠት በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርግ ታይቷል። ወደፊት እየተጠጋ መጫወት የሚወደውን ጋቶች ፓኖምንም በነጻነት ወደ ፊት እና ወደ ኋላ እየተንቀሳቀሰ እንዲጫወት መንገዱን የጠረገለት ሲሆን በአጠቃላይ ኳስን በማስጣልና በመንጠቅ በኩል ጠንካራ ሆኖ አምሽቷል።
Ethiopia Vs Niger


ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ የፈረሰኞቹ ግዙፍ ሰው ኳስን በማደራጀት በኩል ክፍተቶች የታዩበት ነበር ማለት ይቻላል። በተለይ በርካታ ኳሶችን ሲነጠቅ የታየበት አጋጣሚ ይበዛ ነበር። ያም ሆኖ ግን ከእረፍት በፊት ሁለት ያለቀላቸውን ኳሶች በአየር ላይ ቺፕ በማድረግ ለበሀይሉ አሰፋ እና ለራምኬል ሎክ ማቀበል ችሎ ነበር። ዳሩ ግን ሁለቱን የተስፋዬ ምቹ ኳሶች መረብ ላይ ማሳረፍ የተሳናቸው ሁለቱ ፈረሰኞች የልጁን ድካም በዜሮ አባዝተውበታል። በአጠቃላይ ግን ተስፋዬ አለባቸው በቅዳሜ ምሽቱ ጨዋታው ቡድኑ እንዲያጠቃ አነስተኛ ሚና መወጣት ቢችልም የግብ ክልሉን ከተከላካዮች ጋር በመሆን በንቃት ሲጠብቅ የታየ ሲሆን በመጠነኛ ጉዳት ተቀይሮ ከሜዳ በመውጣቱ በአስራት መገርሳ ተተክቷል።

የተጋጣሚን ተከላካይ የማስከፈት ችግር

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌም ሆኑ በስታዲየም የተገኙ ተመልካቾች በግልጽ መናገር የሚችሉት የዋልያዎቹ አማካይ አጥቂዎች እና አጥቂው ታፈሰ ተስፋዬ የተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮችን ጥሶ በማለፍ በኩል ያደረጉት ጫና እምብዛም ሆኖ ታይቷል። በተለይ በሁለቱም የክንፍ መስመሮች የሚጫወቱት ሁለቱ ፈረሰኞች በሀይሉ አሰፋ እና ራምኬል ሎክ የተጋጣሚን ቡድን ተከላካዮች ከማስጨነቅ ይልቅ “የሚይዟቸውን ኳሶች በሙሉ” በሚያስብል መልኩ ለተቃራኒ ቡድን ተከላካዮች በቀላሉ ያስረክቧቸው ነበር። ይህ ድክመታቸው ደግሞ በተለይ በአማካይ ተከላካዩ ላይ ጫና በዝቶበት እንዲያመሽ ያደረገ ሲሆን የኒጀር ተከላካዮችም በነጻነት እንዲጫወቱ በር ከፍተውላቸዋል።

ከሁለቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ አጥቂዎች በተጨማሪም የሴካፋው ኮከብ ተጫዋች ኤሊያስ ማሞ በትናንቱ ጨዋታ ላይ መጠነኛ መቀዛቀዝ የታየበት ሲሆን ጋቶች ፓኖምም ቢሆን ወደ ፊት የሚያሻግራቸው ኳሶች አድራሻቸውን ያላወቁ ነበሩ።

የቅያሪው ውጤት

ለ65 ደቂቃዎች ማራኪ የኳስ ጨዋታ ማሳየት ያልቻሉት የዮሐንስ ሳህሌ ልጆች የኳስ ቁጥጥሩን በስራቸው ማድረግ የቻሉት በሀይሉ አሰፋ እና ተስፋዬ አለባቸው ተቀይረው ከወጡ በኋላ ነበር። የወዳጅነት ጨዋታ በመሆኑ በርካታ ተጫዋቾችን ቀይረው ማስገባት ይችሉ የነበሩት አሰልጣኙ ሶስት ተጫዋቾችን ብቻ ቀይረው ያስገቡ ቢሆንም ተቀይረው የገቡት ተጫዋቾች ግን በጨዋታው ላይ ለውጥ መፍጠር ችለዋል። በተለይ በሀይሉ አሰፋን ቀይሮ የገባው ጥበበኛው ታደለ መንገሻም ሆነ ተስፋዬን የተካው የዳሽን ቢራው አስራት መገርሳ በጨዋታው ላይ የኳስ ቁጥጥሩን ዋልያዎቹ እንዲቆጣጠሩት በማድረግ በኩል የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነበር።

ታደለ መንገሻም ሆነ አስራት መገርሳ ኳስን ይዘው መጫወት የሚወዱ ተጫዋቾች በመሆናቸው ኳስ እግራቸው ስር ሲገባ ምን ማድረግ እንዳለባቸው በሚገባ የሚያውቁ በመሆኑ የተጋጣሚዎቻቸውን ድክመት በሚገባ ማወቅ ችለዋል። ዘግይቶ የገባው የመከላከያው ሙሉዓለም ጥላሁንም ቢሆን በኒጀር ተከላካዮች ላይ የወሰደው የበላይነት መልካም የሚባል ነበር። ዋልያዎቹ አቻ የሆኑበትን ጎል ያስቆጠሩትም ሙሉዓለም ተጠልፎ የተሰጠውን ቅጣት ምት ለቡድን አጋሮቹ ታደለ መንገሻ ያሻማውን ቅጣት ምት የኒጀር ተከላካዮች በእጃቸው በመንካታቸው ነው።

ተከላካይ ክፍሉ

ሳላዲን ባርጌቾን በጉዳት ያጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተከላካይ መስመር ለአስቻለው ታመነ ሁነኛ አጣማሪ እስካሁን ያገኘ አይመስልም። በትናንቱ ጨዋታም አሰልጣኙ ከአስቻለው ታመነ ጋር የዳሽን ቢራውን ያሬድ ባዬህን ያጣመሩ ቢሆንም ያሬድም በእለቱ እንቅስቃሴዎቹ ሁሉ ለስህተት የቀረቡ ነበሩ ማለት ይቻላል። ያሬድ ከአጥቂዎች ጋር አንድ ለአንድ ሲገናኝ የሚደናገጥ ሲሆን ኳስን አረጋግቶ በማስጀመር በኩልም ድክመቶች ነበሩበት።

አንጋፋው ተከላካይና የቡድኑ አምበል ስዩም ተስፋዬ እና ወጣቱ ተካልኝ ደጀኔ የነበራቸው ብቃት ግን አስገራሚ ነበር። ሁለቱ የደደቢት ልጆች ኳሷን ይዘው በሜዳው ኮሪደሮች ሲበሩ መልካም የነበሩ ሲሆን ከተጋጣሚ የሚሰነዘባቸውን ጫናም በቀላሉ መመከት ሲችሉ ታይተዋል። በእለቱ ከሁሉም የተከላካይ ክፍልም ሆነ ከግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ሁሉ በላይ ጥሩ ሆኖ ያመሸው አዲሱ ፈረሰኛ አስቻለው ታመነ ነው። የዲላው ተወላጅ እንደለመደው ኳስ ተቆጣጥሮ ሲጫወት ምርጥ ሲሆን የኋላ ክፍሉን በማደራጀት በኩልም ሆነ ኳስ ይዞ ወደ ፊት በመሄድ ጠንካራ ነበር። አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌም በትናንቱ ጨዋታ ቢያንስ ከእረፍት መልስ ወይም ጨዋታው ሊጠናቀቅ የ30 ደቂቃዎች ጊዜ ሲቀሩ ከአስቻለው ታመነ ጋር አዲሱን የቡና ተከላካይ ወንድይፍራው ጥላሁንን ቢያስገቡት መልካም ይሆን ነበር።

 

የኒጀሮች አጨዋወት

በአዲስ አበባ ስታዲየም ከተካሄዱ ጨዋታዎችም ሆነ ለጨዋታ ከተጋበዙ ቡድኖች በሙሉ የጨዋታ ዲስፕሊን የሌለው የመጀመሪያው ቡድን ቢኖር የትናንቱ የኒጀር ብሔራዊ ቡድን ነው ማለት ይቻላል። ቡድኑ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ በጨዋታ ጥሩ ያልነበረ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ተጫዋቾቹ ሜዳ ላይ ያሳዩት የነበረው ድርጊት ደጋፊውን ያሳዘነ እግር ኳስንም ቢሆን የሚጎዳ ድርጊት ነበር። ኒጀርም ሆነች ኢትዮጵያ በሩዋንዳው የቻን ውድድር ላይ ተሳታፊ በመሆናቸው የወዳጅነት ጨዋታ የተዘጋጀ ቢሆንም የኒጀር ተጫዋቾች ግን ጨዋታውን በሚገባ ተጠቅመው ድክመታቸውንና ጥንካሬያቸውን ከማየት ይልቅ የተጋጣሚዎቻቸውን ተጫዋቾች ሆን ብለው ለመስበር መሞከር፣ ሰዓት ለማባከን በሆነ ባልሆነው ሜዳ ላይ መተኛት፣ የዳኛን ውሳኔ በመቃወም ዳኛ ላይ ምራቅ መትፋት፣ የተጋጣሚ ተጫዋቾችን በጥፊና በቦክስ ሲማቱ፣ ምራቅ ሲተፉ እና ሲሳደቡ  ታይተዋል።

ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ለሚፈጽሙት ጥፋት የሚተላለፈውን የዳኛ ውሳኔ ሲቃወሙ የሚያሳዩት ያልተገባ ድርጊት ደጋፊውን ያበሳጨ ነበር። በተለይ ኳስ በእጅ በመንካታቸው ፍጹም ቅጣት ምት ሲሰጥ ዳኛውን ለመደባደብ ያደረጉት ሙከራ በኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ገላጋይነት ከድብድብ የተመለሱ ቢሆንም ጨዋታውን አቋርጠን እንወጣለን ብለው ሞክረውም ነበር። በእለቱ ከአስር ያላነሱ ተጫዋቾች የቢጫ ካርድ ሰለባ ሲሆኑ አንደ ተጫዋቻቸው ደግሞ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሊባረር ችሏል። በአጠቃላይ የኒጀር ተጫዋቾች ሜዳ ላይ ያሱ የነበረው ባህርይም ሆነ ድርጊት “አሳዳጊ የበደለው መደዴ ልጅ” ባህርይ እንጂ ከፕሮፌሽናል ተጫዋች የሚጠበቅ አልነበረም።  

በዚህ የተጫዋቾች ድርጊት ተበሳጭተው ሳይሆን አይቀርም አሰልጣኙ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ከባድ ልምምድ እንዲሰሩ አድርገዋቸዋል። ጨዋታውን የተመለከቱት በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደርም ብስጭታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል። ኒጀሮች በቻን ዋንጫ እንደ ናይጀሪያ አይነት ጠንካራ ቡድን ውስጥ የተመደበች በመሆኑ ለዚያ ውድድር የወደዳጅነት ጨዋታውን እንደ ስሙ በወዳጅነት ስሜት በመጫወት ድክመትና ጥንካሬያቸውን ለማወቅ ከመሞከር ይልቅ አላስፈላጊ ድርጊት ሲፈጽሙ ማምሸታቸው ከአንድ የአፍሪካ ዋንጫ ተወዳዳሪ ቡድን የማይጠበቅ አስነዋሪ ስራ ሆኖ አይተነዋል።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!