ተጋጣሚ ቡድን ያላገኙት ዋልያዎቹ ለሁለት ተካፍለው ግጥሚያ አካሄዱ
ጥር 03, 2008

በይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የፊታችን ሀሙስ ረፋዱ ላይ ወደ ኪጋሊ ያቀናል። ቡድኑ ወደ ኪጋሊ አቅንቶ በአራተኛው የቻን ዋንጫ ውድድር ላይ ከመካፈሉ በፊት በአገር ውስጥ የሚያደርገውን ልምምድ በወዳጅነት ጨዋታ ለመፈተን ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል። በዚህም መሰረት የመጀመሪያ የአቋም መለኪያ የወዳጅነት ጨዋታውን ከኒጀር አቻው ጋር አከናውኖ አንድ እኩል በሆነ ውጤት ያጠናቀቀ ሲሆን በዚያ ጨዋታ አሰልጣኙ የፈለጉትን ግብ እንዳላገኙ መግለጻቸውም ይታወሳል።

አንድ ተጨማሪ የወዳጅነት ጨዋታ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአጭር ጊዜ ውስጥ የወዳጅነት ጨዋታ የሚያካሂድ ብሔራዊ ቡድን ባለማግኘቱ ያሰበው ሳይሳከለት እንደቀረ ተረጋግጧል። ሆኖም አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የመጀመሪያ ተሰላፊዎቻቸውንና የሚጠቀሙትን የተጫዋቾች ጥምረት ለማወቅ ቡድናቸውን ከሁለት ከፍለው አጫውተዋል።

አሰልጣኙ ቡድናቸውን ለሁለት ከፍለው ባጫወቱበት የእርስ በእርስ ግጥሚያ አሰላለፉን ስንመለከት አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በውድድሩ በቋሚነት የሚያሰልፏቸውን ተጫዋቾች የሚጠቁም ሆኗል። አሰልጣኙ በውድድሩ 4 2 3 1 አሰላለፍ እንደሚጠቀሙ የሚጠበቅ ሲሆን በዚህም የቅዱስ ጊዮርጊሱን አማካይ ተከላካይ ተስፋዬ አለባቸውን ከኢትዮጵያ ቡናው ጋቶች ፓኖም የሚያጣምሩበት የአማካይ ተከላካይ ክፍል እንደሆነ የሚጠቁም ሆኗል። አሰልጣኙ ባለፈው ቅዳሜ አመሻሹ ላይ ከኒጀር ጋር ሲጫወቱ የተጠቀሙበትን ቋሚ አሰላለፍ በዛሬው ጨዋታም በአንድ ላይ ማሰለፋቸው ነው ይህንን ጥቆማ ለማወቅ የተቻለው።

አሰልጣኝ ዮሃንስ ከሁለቱ አማካይ ተከላካዮች ፊት ለፊት ኳስ አቀጣጣዮቹን ቢኒያም በላይን እና ኤሊያስ ማሞን ቻን ላይ እንደiሚጠሚቀሙ የሚጠበቅ ሲሆን በእርስ በእርስ ጨዋታውም ሁለቱን አማካዮች አንድ ላይ አሰልፈዋል። አራተኛው የቻን ዋንጫ የፊታችን ቅዳሜ ጥር 7 ቀን ጀምሮ እስከ ጥር 19 ቀን የሚካሄድ ሲሆን ካፍም ለውድድሩ ሶስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ለሽልማት ማዘጋጀቱ ታውቋል።

እንደ ካፍ ኦንላይን ዘገባ ከሆነ በውድድሩ የዋንጫ ባለቤት የሚሆነው ቡድን 700 ሺህ ዶላር የሚሸለም ሲሆን የፍጻሜ ተፋላሚ ሆኖ የብር ሜዳሊያ የሚያጠልቀው ቡድን የ400 ሺህ ዶላር ተሸላሚ ይሆናል። የካፍ የሽልማት አሰጣጥ የሚያመለክተው የግማሽ ፍጻሜ ተፋለሚዎቹ እያንዳንዳቸው የ250 ሺህ ዶላር ሽልማት የሚበረከትላቸው ሲሆን የሩብ ፍጻሜ ተፋላሚዎቹ ደግሞ 175 ሺህ ዶላር ይሰጣቸዋል። ከምድባቸው ሶስተኛ ወጥተው ያጠናቀቁት 125 ሺህ ዶላር እና የምድባቸውን ግርጌ ይዘው ያጠናቀቁት ደግሞ የ100 ሺህ ዶላር ሽልማት ይበረከትላቸዋል። ኢትዮፉትቦል ዶትኮም ዝግጅት ክፍልም ለዋልያዎቹ መልካም እድልን ይመኛል።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!