“ተጋጣሚዎቻችን ከእኛ የተሻሉ ስለነበሩ ልንሸነፍ ችለናል” አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ
ጥር 20, 2008

በይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሩዋንዳ እየተካሄደ ባለው አራተኛው የቻን ዋንጫ ውድድር በጊዜ ከምድቡ መሰናበቱን ተከትሎ ቡድኑ ትናንት አዲስ አበባ ገብቷል። ቡድኑ በሩዋንዳ ስለነበረው ቆይታ እና አጠቃላይ ስለ ውድድሩ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ እና የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ትናንት ማምሻውን በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በጋዜጣዊ መግለጫው በርካታ ጥያቄዎች በተለይ ለአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የቀረቡላቸው ሲሆን አሰልጣኙም ከቀድሞው ጊዜ በተለየ ተረጋግተው መልስ ሰጥተዋል። የፌዴራሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የቴክኒክ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ “በውድድሩ መሳተፋችንን እንደ ጥሩ አጋጣሚ እናየዋለን። ከአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ስንብት በኋላ የብሔራዊ ቡድናችን ደረጃ እየወረደ ስለነበረ ለቻን ውድድር ማለፋችን መልካም አጋጣሚ ነው። ምክንያቱም እንደ አልጄሪያ ግብጽ ጋና እና ሊቢያ አይነት ቡድኖች በውድድሩ መሳተፍ ሳይችሉ ሲቀሩ እኛ ግን በካፍ መመዘኛ ከ16ቱ የአፍሪካ ምርጥ ቡድን ሆነን በውድድሩ መሳተፋችን ጥሩ አጋጣሚ ነው” ብለዋል።

አቶ ዘሪሁን አያይዘውም ብሔራዊ ቡድኑ ወደ ውድድሩ ከማቅናቱ በፊት ያደረገውን ዝግጅትም ተመልክተዋል። ዝግጅትን በተመለከተ ሲናገሩም “ፕሪሚየር ሊጉ በጣም ዘግይቶ ስለተጀመረ ተጫዋቾችን የመምረጫ ጊዜ አጭር ነበረ። እንዲያም ሆኖ ተጫዋቾች ተመርጠው ዝግጅት የተጀመረ ሲሆን ቡድኑ በውድድሩ ጠንካራ ተፎካካሪ እንዲሆን የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማካሄድ ፌዴሬሽኑ ጥረት አድርጎ ነበር። አንዳንድ አገሮች የሚጠይቁት ከፍተኛ የሆነ ክፍያ እና አንዳንዶቹ ደግሞ ወደ ውድድር ለመሄድ በተዘጋጀንበት ወቅት ፈቃዳቸውን በመግለጻቸው ብሔራዊ ቡድናችን አንድ የወዳጅነት ጨዋታ ብቻ አድርጎ ነው ወደ ሩዋንዳ ያቀናው” ሲሉ ተናግረዋል።

ብሔራዊ ቡድኑ በሩዋንዳ ያደረጋቸውን ሶስት ጨዋታዎች የተነተኑት አቶ ዘሪሁን “በተለይ ኮንጎዎች አሳምነው ነው ያሻነፉን” ብለዋል። በአጠቃላይ ብሔራዊ ቡድኑ የተደለደለበት ምድብም ከባድ ምድብ መሆኑን ተናግረዋል። ውድድሩም ትምህርት ሆኖናል ሲሉ አስተያየታቸውን አጠቃለዋል።

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በበኩላቸው “ተጋጣሚዎቻችን ከእኛ የተሻለ ተዘጋጅተው ስለነበረ ከእኛ የተሻለ ውጤት አስመዝግበዋል። በእኛ በኩል 90 ደቂቃ ሙሉ ከኳስ ጋርም ሆነ ያለ ኳስ ተሯሩጦ በመጫወት በኩል ድክመት ነበረብን። በአጠቃላይ ተጋጣሚዎቻችን በተለይ ኮንጎ ያሸነፈን ከእኛ የተሻለ በመሆኑ ነው” ያሉ ሲሆን አያይዘውም ቡድናቸው ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ መሄዱን ተናግረዋል። በተለይ ከአንጎላ ጋር በነበረው ጨዋታ ቡድኑ ካላፉት ሁለት ጨዋታዎች የተሻለ እንደነበረ ተናግረዋል።

አሰልጣኝ ዮሃንስ “በቻን ከተሳተፉት 16 ቡድኖች በፊፋ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ የመጨረሻውን ደረጃ ይዘን ወደ ውድድር የገባነው እኛ ነበርን” ያሉ ሲሆን አያይዘውም “ተጫዋቾችን መርጠን የህክምና ምርመራ አካሂደን የመጨረሻ ቡድናችንን ይዘን ወደ ውድድር ቦታው ለመሄድ የነበሩን አስር ቀናት ብቻ ነበሩ። ለውጤታችን አለማመር ያ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል። በተለይ አንዳንድ ተጫዋቾቻችን ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ውጭ ሆነው ረጅም ዓመት ስለቆዩ የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ እንዲያገኙ እድል አልነበረነም” በማለት የወዳጅነት ጨዋታ እድል አለመፈጠሩን ኮንነው ተናግረዋል።

የጋዜጣዊ መግለጫውን ሙሉ ክፍል እና ለአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የተሰነዘሩትን ጥያቄዎችና መልሶቻቸውን ይዘን እንመለሳለን።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!