“በእግር ኳስ ሳይንስ ከአንተ የተሻለ ቡድን ሲያሸንፍህ ማመን አለብህ እንጂ በጀብደኝነት ለምን ተሸነፍኩ ልትል አይገባም” አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ
ጥር 20, 2008


በይርጋ አበበ

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ትናንት አመሻሹ ላይ ከፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና በአራተኛው የቻን ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቡድን መሪ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ጋር በመሆን የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ የመጀመሪያ ክፍል ማቅረባችን ይታወሳል። በዚህ ክፍል ደግሞ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ከጋዜጠኞች ለአሰልጣኙ ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል ለአንባቢያን እና ለእግር ኳሱ የሚበጁትን ከእነ መልሶቻቸው ይዘን ቀርበናል።

ጥያቄ፦ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ስራ እንደተረከቡ የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደገለጹት ብሔራዊ ቡድኑ ውጤቱ ጥሩ ካልሆነ ከማንም ሳልጠብቅ ስራዬን እለቃለሁ ብለው ነበር። አሁን ያስመዘገቡት ውጤት ከስራዬ እንድለቅ ያደርገኛል ብለው ያስባሉ? መቼ ነውስ ኃላፊነተዎን የሚለቁት?

መልስ፦ አዎ ብያለሁ አሁንም እላለሁ። ነገር ግን ውሉ ላይ የተቀመጠውም ሆነ በዚያን ወቅት እኔ የተናገርኩት ከነበረው የተሻለ ካላመጣሁ ነበር ያልኩት። ብሔራዊ  ቡድኑን ስረከብ ከነበረው ውጤት የተሻለ ካላመጣሁ ቦታውን በፈቃዴ እለቃለሁ ብያለሁ። ውጤቱን ስንመለከትም ብሔራዊ ቡድኑ ከእኔ በፊት በሴካፋ የነበረው ውጤት ከሩብ ፍጻሜ የዘለለ አልነበረም አሁንስ ካልን ግማሽ ፈጻሜ ተፋላሚ ሆነናል። ስለዚህ ከነበረው ይሻላል ማለት ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ለፌዴሬሽኑ ያስገባሁት ሁለት ቡድን እንዲዘጋጅልኝ ነበር። ነገር ግን ይህ ስላልሆነ በሴካፋ ወጣቶችን እድል በመስጠት እስከተቻለን ድረስ ደግሞ ውጤቱን ጥሩ ለማድረግ ተጫውተናል።

ሌላው በቻን የተቀመጠልኝ መስፈርት ደግሞ ቡድኑን ለውድድሩ ማስገባት የሚል ነበር። ቡድኑን ለቻን ማሳለፍ ችያለሁ። አሁንም ቢሆን ቡድኑ በቻን ያስመዘገበው ውጤት በፊት ከነበረው የተሻለ ነው። ይህ ያረካሃል ወይ? ካላችሁኝ አያረካኝም። የተሻለ ብሰራ ደስ ይለኛል። ፌዴሬሽኑ ያስቀመጠልኝ የውል ኮንትራት ተፈጻሚ አድርጌያለሁ። ስለዚህ ይህንን ነበር ያስቀመጥኩት ይህንም አሳክቻለሁ።

ጥያቄ፦ ሶስቱንም ጨዋታዎች ቡድነዎት እየተሻሻለ መሄዱን ገልጸውልናል። ነገር ግን እኔ በግሌ የፕሮ ዞን ስታቲስቲክሶችን ስመለከት ቡድኑ በሙከራም ሆነ በተለያዩ መመዘኛዎች በተለይ በማጥቃቱ በኩል የነበረው እንቅስቃሴ ዝቅተኛ እንደነበረ ነው። ይህን እንዴት ያዩታል?

መልስ፦ ለፕሮ ዞን የሰጠሁትን ማብራሪያ እኛ የራሳችንን እድገት ከጨዋታ ጨዋታ እያንዳንዱ የቡድኔ ተጫዋች መሻሻል ማሳየቱን ነው የገለጽኩት። ተጫዋቾቼ ምን ያህል ወደ ፊት ኳስች አሻገሩ ክሮሶች ላይ የነበራቸው ሪከርድ ምን ይመስላል እና በመከላከልና በማጥቃት የነበራቸውን አስተዋጽኦ ነው የለካሁት። በዚህ መመዘኛ መሻሻሎች ታይተዋል።

ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ በመጨረሻው ጨዋታ ላይ ከካሜሩን እና ዴሞክራቲክ ኮንጎው ጨዋታችን በበለጠ ክሮሶችን አድርገናል። የተሻሉ የጎል ሙከራዎችን አድርገናል። ይህ ማለት ግን እነሱን በልጠናል ማለት አይደለም። ለምሳሌ በዴሞክራቲክ ኮንጎው ጨዋታ ሙከራ አላደረግንም በካሜሩን ጨዋታ ደግሞ ሙከራ አድርገናል። በአንጎላው ጨዋታ ደግሞ ጎል አስቆጥራል።
በኳስ ቁጥጥሩ በኩልም ቢሆን ከመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በተለየ በመጨረሻው ጨዋታ ከተጋጣሚያችን በብዙም ሳንበለጥ ነው የተጫወትነው። በሌሎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግን በደንብ እየተበለጥን ነው የተሸነፍነው።
ጥያቄ ለአንድ ድረ ገጽ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ቃል በቃል ያነበብኩትን ልንገረዎት በተሰጠኝ ኃላፊነት ላይ በሚገባ መስራት ችያለሁ። ወደ ኢትዮጵያ ስመለስ ከኃላፊነቴ ልወርድ እችለለሁ ብለዋል። ይህ ምን ማለት ነው?

መልስ፦ እኔ በግልጽ የሰጠሁት ቃለ ምልልስ የለም። የሰጠሁት መግለጫ ካፍ ባዘጋጀልኝ እድል መሰረት ፕሬስ ኮንፈረንስ ነው የሰጠሁት እንጂ ለማንም በግል የሰጠሁት መግለጫ የለም። የኔ መግለጫ ተብሎ ያነበብከው ያልተናገርኩትን ነው። ስለዚህ በዚህ ላይ መልስ ልሰጥበት አልችልም። 

ጥያቄ፦ አሰልጣኝ ዮሃንስ በቻን ያደረጋችሁትን ቆይታ በተመለከተ በውጤቱ አልተከፋሁም ብለዋል። መሬት ላይ የተመዘገበውን ውጤት ከተመለከትን ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑ አምስት ጎል ገብቶበት አንድ ጎል ብቻ አስቆጥሮ ከምድቡ ግርጌ ላይ ተቀምጦ ነው የተመለሰው። ይህ ውጤት ካላሳዘነዎት ብሔራዊ ቡድኑ ምን ቢገጥመው ነው የሚያሳንዘዎት?

መልስ ፦ በውጤቱ አላዘንክም ላልከኝ አዎ አላዘንኩም። በውጤቱ አላዘንኩም ማለት ግን ደስተኛ ነኝ ማለት አይደለም። በውጤቱ ያለዘንኩበት ምክንያት አንደኛ ከአገራችን ተጨባጭ የእግር ኳስ ሁኔታ ብንሄድ እኔ ከዚህ ቦታ ላይ ከተቀመጥኩ ስምንተ ወራትን አስቆጥሬያለሁ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ለተሰራው ስራ እኔ ልጠየቅ እችላለሁ። በአጠቃላይ የአገራችን እግር ኳስ ስላለበት ሁኔታ ግን ልጠየቅ አይገባም። ይህን ያልኩበት ምክንያት ምንድን ነው? የእኛ ተጋጣሚ አገሮች እነ ማን ናቸው ብለን ስንጠይቅ በፊፋ ደረጃ ከ50 እና ስልሳ በላይ ናቸው። እኛስ ስንል 118ኛ ላይ ነን። የእኛ ልጆች ከእነዚህ በቡድኖች ጋር ተጫውተው ባስመዘገቡት ውጤት ላዝን አይገባም። ነገር ግን ደስተኛ ነኝ ማለት አይደለም። እነሱን ብናሸነፍ ደስ ይለኝ ነበር። ነገር ግን አልሆነም።

የእግር ኳስ ሳይንስ ደግሞ ከአንተ የተሻለ ቡድን ሲያሸንፍ ማመን አለብህ እንጂ በጀብደኝነት ለምን ተሸነፍኩ ልትል አይገባም። ከዚያ በበለጠ መሸነፍህን ማመን አለብህ። ደረጃቸውም የሚያሳየው ይህንኑ ነው። ከዓለም እግር ኳስ ደረጃ ከእኛ የበለጡ ቡድኖች ቢያሸንፉን ልጆቹ ላደረጉት ጥረት ለምንድን ነው ምስጋና የማይኖረኝ? ጅቡቲ ወይም ሶማሌ ቢያሸንፈን ኖሮ አፕሪሼት ላደርግ አልፈልግም ነገር ግን ያሸነፉን ከእኛ የሚበልጡ ቡድኖች ናቸው። ስለዚህ ነው አፕሪሼሽን መስጠት የፈለኩት። ስለዚህ እኛ በእግር ኳስ ደረጃችን የት ነው ያለነው? ማን ነን? ምን ያህልስ ነው የሰራነው? ምን ያህል ነው የተዘጋጀነው? ምን ያህል ወጣቶችን ተተኪዎችን አዘጋጅተናል? ዝግጅትስ ቢሆን ሌላው ዓለም እንደሚዘጋጀው ነው ወይስ ምን አይነት ዝግጅት ነው የምናደርገው? ይህንን ነው መወያየት የሚገባው። የምንጠይቀው ጥያቄ እና የምንፈልገው ውጤት ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አብሮ ይሄዳል ወይ? ለምሳሌ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ካሜሩንን ማሸነፍ አለበት ስንል እኛ ማን ስለሆንን ነው ማሸነፍ የሚገባን? ብለን መጠየቅ አለብን። ስንሸነፍም ምን ስለሆንን ነው የተሸነፍነው? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። እነኝህ ነገሮች ሊነሱ ይገባል።

ጥያቄ፦ ተጫዋቾቼ የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ የላቸውም ብለዋል። ነገር ግን ቡድኑን ማሰልጠን ከጀመሩበት ካለፉት ስምንት ወራት ጀምሮ ወደ ቻን ከማቅናተዎ በፊት 18 የተለያዩ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችነ አድርገዋል። በቻን የተጠቀሙባቸው ተጫዋቾች ደግሞ አብዛኞቹ ቡድኑን ሲረከቡ ጀምሮ የነበሩትን ነው። በዚያ ላይ ከኒጀር ጋር ባደረጋችሁት ጨዋታ 13 ተጫዋቾችን ብቻ ነው መጠቀም የቻሉት። ይህ በራሱ አይጣረስም ወይ?

መልስ ፦ በዚህ ጉዳይ ላይ የተግባባን አልመሰለኝም። ማለት የፈለኩት አዲስ የመረጥናቸው ልጆች ነበሩ ለረጅመ ጊዜ ኢንተርናሽናል ውድድር ያላደረጉ። ለምሳሌ ተስፋዬ አለባቸውን እናንሳ። ተስፋዬ ከሶስት ዓመታት ወዲህ ኢንተርናሽናል ጨዋታ አላደረገም። ታፈሰ ተስፋዬም ቢሆን ከስምንት ዓመት በላይ ሆኖታል ለብሔራ ቡድን ከተጫወተ። እኔ ማለት የፈለኩትም ለብሔራዊ ቡድነ ተጫውተው አያውቁም ሳይሆን በአሁኑ ወቅት የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ የላቸውም ነው እንጂ ለብሔራዊ ቡድን ተጫውተው አያውቍም ማለት አይደለም።
በኒጀሩ የወዳጅነት ጨዋታ ለምን 13 ተጫዋቾችን ብቻ ተጠቀማችሁ ላልከው በወቅቱ እኔ ያሰብኩት ሁለተኛ የወዳጅነት ጨዋታ እንደምናካሂድ ነበር ከፌዴሬሽኑ የተነገረኝ። ነገር ግን ቅድም አቶ ዘሪሁን እንዳሉት አንዳንዶቹ ከፍተኛ ገንዘብ በመጠየቃቸው አንዳንዶቹ ደግሞ ወደ ውድድሩ ቦታ ልናቀና በምንዘጋጅበት ወቅት ፈቃደኝነታቸውን በመግለጻቸው ሌላ የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግ አልቻልንም።

ጥያቄ፦ እርሰዎ ብሔራዊ ቡድኑን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ በብድኑ ውስጥ የተመለከቱት 
ጥንካሬ ምንድን ነው?

መልስ ፦ በቡድኑ ላይ የተመለከትኩት ጠንካራ ጎን የመጀመሪያው የተጫዋቾች ዲሲፕሊን መሻሻሉን ነው። ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ ከ20 በላይ ጨዋታዎችን አካሂደን አንድ ተጫዋች ብቻ ነው በቀይ ካርድ የተሰናበተው። ባልሳሳት በአገራችን ብሔራዊ ቡድን ታሪክ ይህ ሪከርድ ሳይሆን አይቀርም።

ሌላው ቡድኑ ላይ ያያሁት ጠንካራ ለውጥ ጫናን መቋቋም መቻላቸው ነው። ለዚህ ምሳሌ ብጠቅስልሽ ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ እና ከብሩንዲ ጋር ባደረግናቸው ጨዋታዎች በሜዳቸው ተሸንፈን የመጣን ቢሆንም በሶስት እና በሁለት ቀናት ዝግጅት ውጤት መቀልበስ ችለናል። ይህ የሚያመለክተው ተጫዋቾቼ በአካል ብቃትም ሆነ በስነ ልቦና ጫናን መቋቋም መቻላቸውን ነው።
ይቀጥላል!!

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
Dear Readers: The views expressed on our comment pages under are the personal views of individual contributors and ethiofootball.com bears no responsibility for what readers post and is not liable for any form of impersonation. also note that while we value your feedback we may block inappropriate comment.
Ashenafi Kebede [753 days ago.]
 አይ ዮሃንስ የምታስቅ ሰው ነህ ሁልጊዜ ከሽንፈትህ በኃላ የምትሰጣቸው ምክንያቶች ያስቃሉ... ያሳዝናሉ ምን ያህል እንደማትችል ያሳብቁብሃልም:: ኳስን መመልከት ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ እንደ አንተ አይነት ኮች ገርሞኝ አስቆኝ አሳዝኖኝ አያውቅም :: አንት እኮ ቡድን መስራት እንኳን እኮ ነው ያልቻልከው ! ልጆቹን እንዴት አድርገህ መጠቀም እንዳለብህ እንኳን አላወክበትም ! ስንት ጊዜ ሆነህ ብሔራዊ ቡድኑን ማሰልጠን ከጀመርክ ? በጣም የሚገርመው ነገር ግን እስካሁን ድረስ ቤስት 11 አይደለም ቤስት 6 ተጫዋቾች እንኳን የሉህም:: ሁሌም ትጠራለህ .... ታባርራለህ ! ትጠራለህ ..... ታባርራለህ ሃ ሃ ሃ “ተጋጣሚዎቻችን ከእኛ የተሻሉ ስለነበሩ ልንሸነፍ ችለናል” አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ሃ ሃ ሃ ሃ እውነታው ግን ተጋጣሚዎቻችን ሳይሆን አሰልጣኞቹ ከአንተ ስለሚሻሉ ልንሸነፍ ችለናል:: አንት እኮ ሴካፋ ላይ ተፎግረሃል በደካማው ቶርናሜንት ያውም እዚሁ ሃገራችን ለይ ተዘጋጅቶ...... ማሸነፍ የቻልከው የሱማሊያን ቡድን ብቻ ነው :: እባክህ ዮሃንስ ጨጓራችንን አትላጠው አታቃጥለው ቦታህን ለሚችል ሰው ዛሬ ነገ ሳትል ልቀቅቅቅቅቅቅቅቅቅቅቅ !!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!

Habetom [753 days ago.]
 ጥያቄ፦ አሰልጣኝ ዮሃንስ በቻን ያደረጋችሁትን ቆይታ በተመለከተ በውጤቱ አልተከፋሁም ብለዋል። መሬት ላይ የተመዘገበውን ውጤት ከተመለከትን ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑ አምስት ጎል ገብቶበት አንድ ጎል ብቻ አስቆጥሮ ከምድቡ ግርጌ ላይ ተቀምጦ ነው የተመለሰው። ይህ ውጤት ካላሳዘነዎት ብሔራዊ ቡድኑ ምን ቢገጥመው ነው የሚያሳንዘዎት? wooooooow what a great question !!! @ ethiofoot ball.com :- pls tell us the journalist name ..... who asked the above Q ?????

 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!