የሀበሻ ቢራ እና ኢትዮጵያ ቡና የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት በእግር ኳሳዊ እይታ
ጥር 27, 2008

በይርጋ አበበ

እግር ኳስ ከስፖርትነት እና መዝናኛነት በዘለለ እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት እና በርካታ ሰዎችን ደግሞ ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘርፍ ሆኗል። ለአብነት ካየን በርካቶቻችን እነደ ራሽን ተሰልፈን ገንዘባችንን ከፍለን የምንመለከታቸው የአውሮፓ ሊጎችን ማንሳት ይቻላል። በታላለቆቹ የአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾች ከክለቦቻቸው የሚከፈላቸው ውርሃዊ ምንዳ ዳጎስ ያለ መሆኑን እናያለን። ክለቦቹ ደግሞ ለተጫዋቾቻቸው የሚከፍሉትን ረብጣ ዶላር ሲያስቡ ከተጫዋቾቹ የሜዳ ላይ ብቃት እና የማስታወቂያ ገቢ በተጨማሪ ሌሎች ተጨማሪ የገቢ ማግኛ መንገዶችን በመጠቀም ራሳቸውን ያጠናክራሉ። ለዚህ የገቢ ማስገኛ መንገድ ደግሞ ቀዳሚ ተመራጭ የሆኑት የቴሌቪዥን ገቢ እና የስፖንሰርሺፕ ስምምነቶች ናቸው።

ከላይ የጠቀስኩት የእግር ኳስ ቢዝነስ በአገራችን ያልተለመደ መሆኑ ግልጽ ነው። ነገር ግን “ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ አይጠፋም” እንዲሉ የሃብታሞቹን አገራት እግር ኳስም ሆነ የእኛን የኢኮኖሚ ድሃዎቹን እግር ኳስ የየሚያመሳስላቸው አንድ ነገር ቢኖር በተመሳሳይ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚተዳደሩ ዘርፎች ነው። ለረጅም ዘመናት ከመንግስት በጀት ድጎማ  እና ቀጥተኛ ተጽእኖ መውጣት ያልቻለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከመንግስት ተጽእኖ መውጣት ባይችል እንኳ ከገንዘብ ድጎማው ለመውጣት እየተፍጨረጨረ ይገኛል። ለዚህ አባባሌ ማስረጃ የሚሆነው የቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡና እና ደደቢት የቅርብ ዓመታት ጉዞ ነው።

ሶስቱ ክለቦች ከመንግስት ድርጅት ነጻ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ገቢያቸውን ለማሳደግና በሊጉም ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ለመቅረብ ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች መካከል የማሊያ ስፖንሰር አድራጊ ድርጅቶች ጋር መዋዋል ነው። ፈረሰኞቹ ከግዙፉ የሲሚንቶ አምራች ካምፓኒ ደርባ ሲሚንቶ ጋር የተዋዋሉ ሲሆን ሰማያዊዮቹ በበኩላቸው መጠኑ ባልተገለጸ ዋጋ ከሌላው የሲሚንቶ ፋብሪካ መሰቦ ሲሚንቶ ጋር ተዋውለዋል። እነዚህ ክለቦች በስፖንሰር ሺፕ ስምምነታቸው መሰረት መጠኑ ጠቀም ያለ ገንዘብ ወደ ካዝናቸው የሚያስገቡ መሆናቸው ይታወቃል። ሰሞኑን ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና ከሀበሻ ቢራ ፋብሪካ ጋር ለአምስት ዓመታት የሚያቆየውን የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ተዋውሏል። ይህን በተመለከተ ከዚህ በታች የሚከተለውን ጽሁፍ አዘጋጅተናል።

የስፖንሰር ሺፕ ስምምነቱ መዘርዝር

የክለቡ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ደሳለኝ ከኢትዮፉትቦል ዶት ኮምጋር በስልክ ባደረጉት ቃለ ምልል “የስፖንሰር ሺፕ ስምምነቱ በዓመት 12 ሚሊዮን ብር ሆኖ በየዓመቱ የገንዘቡ መጠን እየጨመረ ለአምስት ዓመታት ይቀጥላል” ብለዋል። የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ጨምረው እንደተናገሩት ስምምነቱ ከገንዘብ ክፍያው በተጨማሪ ክለቡ በሚያዘጋጃቸ ፕሮግራሞች ሁሉ ቢራ ፋብሪካው ስፖንሰር የሚያደርግ ይሆናል። ለክለቡ ዋናው ተተኪው ታዳጊውና ሴቶች ቡድን ለእያንዳንዱ ሶስት ሶስት አይነት ኦሪጂናል ማሊያዎችን ከአዲዳስ ካምፓኒ ጋር ተነጋግሮ የሚያስመጣውም ቢራ ፋብሪካው ይሆናል። ይህ ማለት ደግሞ ለማሊያ ብቻ በዓመት ከሶስት ሚሊዮን ብር የማያንስ ወጪ ያወጣል ማለት ነው።

ሁለቱ ወገኖች የፊርማ ስነ ስርዓታቸውን ያከናወኑት በግሎባል ሆቴል መሆኑን የገለጹት አቶ ሙሉጌታ በእለቱም ከ200 በላየ የክለቡ ደጋፊዎች ተገኝተዋል ብለዋል። ስምምነቱን የፈረሙት በክለቡ በኩል የክለቡ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ እና በሀበሻ ቢራ በኩል ደግሞ የድርጅቱ ማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ታዲዮስ ኩርፉ ናቸው።

የስምምነቱ እግር ኳሳዊ ትርፎች

ላለፉት ሁለት ዓመታት እና ከዚያ በላይ በግንባታ ላይ የነበረው የቡና ክለብ የስፖርት ማዕከል 10.2 ሚሊዮን ብር ከወጣበት በኋላ ግንባታው ተጠናቆ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ተጫዋቾችን መቀበል እንደሚችል ተነግሯል። የስፖርት ማዕከሉ 60 የተጫዋቾች ማደሪያ ዶርምን ጨምሮ የፊዚዮ ቴራፒ ማዕከል ቢሮዎች ጂምናዚየም እና አዳራሾችን የያዘ መሆኑንም አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል።

የክለቡ ስፖርት ማዕከል ግንባታው መጠናቀቁት ተከትሎ ክለቡ የስፖርት ማዕከሉ በሚገኝበት ቦታ የራሱ ስታዲየምና የመለማመጃ ሜዳ ሊገነባ ነው። ቡና ይህንን ግንባታ ለማካሄድ ከሚያስፈልገው ከፍተኛ ወጪ የተነሳ ከሀበሻ ቢራ ጋር የደረሰበት የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ሌሎች ወጪዎችን ወደ ግንባታው እንዲያዞር ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል። በዓመት ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ለክለቡ መመደብ ያልቻለው ቡና ስፖርት ክለብ የአሁኑ ስፖንሰር ሺፕ ስምምነት በጀቱን ከፍ የሚያደርግለት መሆኑ ይታወቃል። በዚህም መሰረት ሜዳ ላይ ከሚያሽቆለቁለው ውጤቱ ለማገገም ጥሩ መስፈንጠሪያ ቦርድ ሊሆንለት ይችላል።

የሀበሻ ቢራ እና ኢትዮጵያ ቡና ስምምነት ከገንዘብም በላይ የክለቡ አመራሮች እድሉን በሚገባ መጠቀም ከቻሉ ለክለቡ እውቅና በር ከፋች ሊሆንለት ይችላል። እንደሚታወቀው ሀበሻ ቢራ ከግዙፉ የሆላንድ ቢራ ጠማቂ ባቫሪያ ጋር በጣምራ የሚሰራ ድርጅት ነው። ሆላንዶች ደግሞ ከቢራ ጠመቃቸው በተጓዳኝ በእግር ኳስ ሳይንስ ላይ ያላቸው እውቀትና ልጠና የተመሰከረላቸው ናቸው። ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ለታዳጊዎች አካዳሚ ዳይሬክተር እንዲሆኑለት ሆላንዳዊውን ሮይ ሂድኒክን በከፍተኛ ገንዘብ ማስመጣቱ አንዱ ማሳያ ነው። ቡናም ከስኬታማዎቹ ሆላንዳዊያን የእግር ኳስ ጠበብቶች ጋር በጣምራ ለመስራት የሚያስችላቸውን እድል እንዲያገኙ ቢራ ፋብሪካው ሊተባበራቸው ይችላል።

ሌላው ደግሞ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ሆላንዳዊያን ቱጃሮች ገንዘባቸውን ኢትዮጵያ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ጀምረዋል። ከአበባ እርሻ እስከ ወተት ኢንዱስትሪ ባሉ ዘርፎች የተሰማሩት ሆላንዳዊያን ወደ አገራቸው ሲመለሱም ሆነ የእነሱን ድርጅቶች ለአገራቸው የመንግስት ባለስልጣናት በሚያስጎበኙበት ወቅት አብሮ የሚያያዘው የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ስም ይሆናል። እነዚህን ሁለት ወርቃማ እድሎች ቡና በአግባቡ መጠቀም ከቻለ ከሆላንድ ክለቦች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ እና የስልጠና ልውውጥ የማድረግ እድሎችን ያገኛል ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ክለቡ ራሱን ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ የሚያስገባበት ሰፊ እና ምቹ ሁኔታ ተፈጠረለት ማለት ነው። ለዚህ ደግሞ የአሁኑን የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት ከገንዘብም በላይ መሆኑን በሚገባ መረዳት ይኖርባቸዋል። 

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!