የጥሎ ማለፉ ሩብ ፍጻሜ የጠንካራዎቹ ፍልሚያ ሆኗል
የካቲት 04, 2008

በይርጋ አበበ

ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተጀመረው የ2008 የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ጠንካራዎቹ ክለቦች ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅለዋል። ሁለት ጨዋታዎች ማለትም ፈረሰኞቹ ከደደቢት እና መከላከያ ከወላይታ ድቻ የሚያካሂዷቸው ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስና መከላካያ አህጉራዊ ውድድሮች ስላሉባቸው ያልተካሄዱ ሲሆን እስካሁን በተካሄዱት አምስት ጨዋታዎች ታላላቆቹ ኢትዮጵያ ቡና፣ ሲዳማ ቡና፣ አዳማ ከነማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለፉ ሲሆን በታደለ መንገሻ አጋፋሪነት ወደ ተፎካካሪነት የተመለሰው አርባ ምንጭ ከነማም ሩም ፍጻሜውን መቀላቀል ችሏል።

ሩብ ፍጻሜውን ከተቀላቀሉት አምስት ክለቦች በተጨማሪ ቀሪዎቹ ሁለት ክለቦች ማለትም ከደደቢትና ቅዱስ ጊዮርጊስ ወይም ከወላይታ ድቻ እና መከላከያ ሁለቱ ሩብ ፍጻሜውን መቀላቀላቸው የማይቀር ሲሆን ይህም የዘንድሮውን ጥሎ ማለፍ ገና በሩብ ፍጻሜው ከፍተኛ ፉክክር የሚታይበት አድርጎታል።

እስካሁን የተካሄዱ ጨዋታዎችን ውጤት ለመግለጽ ያህል

ያለፈው ዓመት የፍጻሜ ተፋላሚ ሀዋሳ ከነማ ከአርባ ምንጭ ከነማ ጋር ተጫውቶ ከሚጠበቀው በታች አቋሙ ወርዶ የታየ ሲሆን በታደለ መንገሻ ብቸኛ ጎል አንድ ለባዶ ተሸንፎ ከውድድሩ ውጭ ሆኗል።

ውጤትና አሰልጣኝ አልበረክትለት ብሎ ባለፉት አራት ዓመታት አምስት አሰልጣኞችን የቀያየረው ኢትዮጵያ ቡና በዚህ ዓመት ፕሪሚየር ሊጉን ከተቀላቀለው ሆሳዕና ሃድያ ጋር ተጫውቶ ያለ ግብ አቻ ቢለያይም አሸናፊውን ለመለየት በተሰጡት መለያ ምቶች አራት ለሁለት አሸንፎ ነው ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀለው። በዚያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ሜዳ ላይ ያሳዩት ብቃት ቡድኑን “ወዴት እየሄደ ነው?” ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድድ ነበር። በርካታ ደጋፊዎችም በክለባቸው ተጫዋቾች ብቃት አዝነው ታይተዋል።

ኤሌክትሪክና አዳማ ከነማ ባካሄዱት ጨዋታ ኤሌክትሪክ ዘንድሮም በጊዜ ከጥሎ ማለፉ ውጭ ሆኗል። በፕሪሚየር ሊጉም ውጤት አልቀናህ ያለው ኮረንቲው ከአዳማ ከነማ ጋር በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንድ ለአንድ የተለያየ ቢሆንም በመለያ ምት ተሸንፎ ከውድድሩ በጊዜ ተሰናብቷል። በዚህም ምክንያት ከሩም ፍጻሜው ጀምሮ ኮረንቲው ስታዲየም አይታይም።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድሬዳዋ ከነማን ሶስት ለባዶ አሸንፎት ወደ ሩብ ፍጻሜ ያለፈ ሲሆን በዚህ ዓመት ሊጉን የተቀላቀሉት ድሬዳዋ ከነማ እና ሆሳዕና ሀድያ በተመሳሳይ ወቅት ከጥሎ ማለፉ ወጥተዋል። ለአሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማሪያም ቡድን ጎሎቹን ያስቆጠሩት ፍሊፕ ዳውዝ እና ሲሳይ ቶላ ናቸው። በተለይ ዳውዝ በዚህ ዓመት የጎሉ መስመር ጠፍቶበት የቆዬ በመሆኑ ድሬዳዋ ላይ ያስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች የጎል ድርቁ እንዲለቀው ያደርጉለታል ተብሎ ይታመናል።

ዳሽን ቢራ በጥሎ ማለፉም አልሳካልህ ብሎታል። በተከታታይ ሁለት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎቹን በሽንፈት ያጠናቀቀው ዳሽን ቢራ ትናንትም በጥሎ ማለፉ ከሲዳማ ቡና ጋር ተጫውቶ ለተከታታይ ሶስተኛ ጊዜ ጎል ሳያስቆጥር በባዶ ተሸንፏል። የተሸነፈው አንድ ለባዶ ሲሆን ጎል ያገባበት ደግሞ የሲዳማ ቡናው የመስመር አማካይ አዲስ ግደይ ነው።

መከላከያ ከወላይታ ድቻ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደደቢት የሚያካሂዷቸው ጨዋታዎች ወደ ፊት የሚገለጹ ይሆናል። በጥሎ ማለፉ አሸናፊ የሚሆነው ክለብ ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ቅድመ ማጣሪያ የመሳተፍ እድል ያገኛል።

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!