የሊጉ ሁለተኛ ዙር ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች
ሚያዚያ 12, 2008

በይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር መርሃ ግብር ነገ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ስድስት ጨዋታዎችን አካሂዶ ዓርብ አመሻሹ ደግሞ አንድ ጨዋታ ያካሂዳል። ሊጉ በሁለተኛው ሳምንት እነማን ይገናኛሉ ጨዋታዎቹስ ምን መልክ ይኖራቸዋል ለሚለው ከዚህ በታች ቀርቧል።

ጨዋታዎቹ

አዲስ አበባ ላይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና ከመከላከያ ይጫወታሉ። በመጀመሪያው ዙር ግንኙነታቸው አንድ ለባዶ ያሸነፈው መከላከያ የሊጉን ሁለተኛ ዙር የጀመረው በመጀመሪያው ዙር አንድ ለባዶ ያሸነፈውን ኤሌክትሪክን ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ነው። በአስተዳደራዊ ጉዳዮችና በደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ደጋፊዎች ካምቦሎጆን የተቃውሞ መድረክ ያደረጉት ቡናዎች በበኩላቸው ባሳለፍነው ሳምንት ንግድ ባንክን አንድ ለባዶ በማሸነፍ ነው ያሳለፉት። ባለሜዳው መከላከያ በ19 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ቡና በበኩሉ በ17 ነጥብ ዘጠንኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ከቡና እና መከላከያ ጨዋታ በኋላ ያለውን ሰዓት ወስደው ካምቦሎጆ ላይ የሚፋለሙት ደግሞ ኤሌክትሪክ እና አዳማ ከነማ ናቸው። ባሳለፍነው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ ከፈረሰኞቹ ጋር ሲጫወቱ ደጋፊዎቻቸው የተጎዱባቸው አዳማ ከነማዎች ከፈረሰኞቹ ላይ አንድ ነጥብ መውሰድ ችለው ነበር። ደረጃቸውንም በ24 ነጥብ ሶስተኛ ላይ እንዲረጋ አድርገዋል። በአንጻሩ ኮረንቲዎቹ ወጥ አቋም ማሳየት ተስኗቸው በመከላከያ ሁለት ለባዶ ተሸንፈው ደረጃቸውን ወደ 11 ዝቅ አድርገዋል። 

ከአዲስ አበባ ውጭ በሚካሄዱ ጨዋታዎች ደግሞ የሊጉ መሪዎችና የ12 ጊዜ አሸናፊዎቹ ፈረሰኞቹ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ተጉዘው ከሲዳማ ቡና ጋር ይጫወታሉ። በመጀመሪያው ዙር ሁለተኛ ሳምንተ ሁለቱ ቡድኖች አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ተጫውተው ቅዱስ ጊዮርጊስ አምስት ለአንድ በሆነ ሰፊ የጎል ልዩነት አስመዝግቦ ነበር ያሸነፈው። ሲዳማ ቡና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፈረሰኞቹን ማሸነፍ ዳገት የሆነበት ይመስላል። ፈረሰኞቹ 30 ነጥቦችን ሰብስበው በሊጉ አናት ላይ ሲቀመጡ ሲዳማ ቡና በበኩሉ 19 ነጥብና ሶስት የጎል እዳ ይዘው ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ድል የቀናቸው ሀዋሳ ከነማ እና ድሬዳዋ ከነማ ሀዋሳ ላይ ይገናኛሉ። ሁለቱ ቡድኖች በአሁኖቹ አሰልጣኞቻቸው እየተመሩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት ባሳለፍነው መስከረም ወር ላይ ተዘጋጅቶ በነበረው የሃዋሳ ሴንትራል ሆቴል ካፕ ላይ ነበር። በነጥብ ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት ደግሞ በሊጉ የመጀመሪያው ዙር ሲሆን አንድ እኩል ነበር የተለያዩት። ለወራት በወራጅ ቀጠና ውስጥ ከርሞ የነበረው የውበቱ አባተ ቡድን 19 ነጥቦችን የዞ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በሜዳው አንድም ቀን የሽንፈት ጽዋን ያልቀመሰው ድሬዳዋ ከነማ በበኩሉ 21 ነጥቦችን ይዞ አምስተኛ ላይ ተቀምጧል። ሀዋሳ ነገ በለስ ከቀናው የድሬዳዋን ደረጃ ይቀበላል።

ከውጤት ጋር መታረቅ የተሳነው የጎንደሩ ዳሽን ቢራ ጎንደር ላይ ሀድያ ሆሳዕናን ያስተናግዳል። ሁለቱ ቡድኖች በደረጃው ግርጌ ላይ ነው የተቀመጡት። ቡድኖቹ በቀጣዩ ዓመት 16 ክለቦች በሚሳተፉበት ፕሪሚየር ሊግ ለመወዳደር በዚህ ዓመት ከመውረድ መትረፍ ግድ ይላቸዋል። ለዚህ ደግሞ የነገው ጨዋታ የህልውና ጉዳይ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

በደቡብ ደርቢ ደግሞ ጎረቤታማቾቹ አርባ ምንጭ ከነማ እና ወላይታ ድቻ አርባ ምንጭ ላይ ይገናኛሉ። ባሳለፍነው ሳምንት ደደቢትን አንድ ለባዶ አሸንፎ ደረጃውን ወደ አራተኛ ያሳደገው ወላይታ ድቻ እና 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው አርባ ምንጭ ከነማ የሚያካሂዱት ጨዋታ በደጋፊዎቻቸው ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ጨዋታ ነው።

የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ የሚካሄደው አርብ አመሻሹ ላይ ነው። ባለፈው ሳምንት የተሸነፉት ንግድ ባንክ እና ደደቢት ከሽንፈት ሀንጎቨር ለመውጣትና ደረጃቸውን ለማሻሻል የሚያካሂዱት ጨዋታ ነው አርብ 11፡30 ላይ ካምቦሎጆ ላይ የሚካሄደው ጨዋታ። ባለፉት አራት ዓመታት ከደደቢት ጋር ስኬታማ ጊዜያትን አሳልፎ በዚህ ዓመት ንግድ ባንክን የተቀላቀለው ሸይቩ ጂብሪል የቀድሞ ክለቡን ለሁለተኛ ጊዜ በተቃራኒነት ይገጥማል። ደደቢት በ25 ነጥብ ሁለተኛ ሲሆን ንግድ ባንክ ደግሞ አስረኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!