ዳሽን ቢራ እግር ኳስ ክለብ የ2008 ዓ.ም ሁለተኛው ከፕሪሚየር ሊግ ተሰናባች ክለብ ሆነዳሽን ቢራ እግር ኳስ ክለብ የ2008 ዓ.ም ሁለተኛው ከፕሪሚየር ሊግ ተሰናባች ክ
ሰኔ 22, 2008

ዳሽን ቢራ እግር ኳስ ክለብ የ2008 ዓ.ም ሁለተኛው ከፕሪሚየር ሊግ ተሰናባች ክለብ ሆነ

አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀዝቀዝ እያለ ሲካሄድ የቆየው የ2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሀድያ ሆሳዕናን እና   ወደ ታችኛው ሊግ አውርዶ ቅዱስ ጊዮርጊስን ደግሞ የዘውዱ ባለቤት አድርጎ ዛሬ ይጠናቀቃል። እስከ ትናንት ምሽት ድረስ ሁለተኛው ወዳቂ ክለብ ሳይታወቅ በቆየበት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ትናንት ከቀኑ 8፡00 በአዳማው አበበ ቢቂላ እና በአዲስ አበባ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰዓት እንዲካሄዱ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በወሰነው ውሳኔ መሰረት ጨዋታዎቹ ተካሂደው ነበር።

አዲስ አበባ ላይ ኤሌክትሪክ ከንግድ ባንክ ጋር ተጫውቶ በፒተር ንዋድኬ ብቸኛ ጎል በማሸነፍ ከመውረድ ሲተርፍ አዳማ ላይ ከሲዳማ ቡና ጋር የተጫወተው ዳሽን ቢራ በኤዶም ሆሶውሮቢ ጎል አማካኝነት ለተከታታይ አምስት ሳምንታት ያልተሸነፈውን ሲዳማ ቡናን ማሸነፍ ቢችልም የመውረድን አስከፊ ጽዋ ከመጎንጨት ግን አልተረፈም። በዚህም ምክንያት ዳሽን ቢራ እግር ኳስ ክለብ ፕሪሚየር ሊጉን በተቀላቀለ በሶስተኛ ዓመቱ ወደታችኛው ሊግ ለመመለስ ተገድዷል።

ከሁለት ወራት በፊት በሜዳው የጎንደሩ አጼ ፋሲል ስታዲየም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረገው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ የቡናን ደጋፊዎች የዳሽን ቢራ ደጋፊዎች በመደባደባቸው ዳሽን ቢራ ቀሪ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎቹን ከሜዳው ውጭ እንዲጫወት ፌዴሬሽኑ ወስኖበት ነበር። በውሳኔው መሰረትም ቀሪ ጨዋታዎቹን በአዳማው አበበ ቢቂላ ስታዲየም እንዲጫወት ፌዴሬሽኑን የጠየቀው ዳሽን ቢራ ጥያቄው ተፈቅዶለት አዳማ ላይ ሲጫወት ቆይቷል። አዳማ ላይ ካካሄዳቸው ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥብ ማግኘት ቢችልም አዲስ አበባ ላይ ከሻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት ጋር ባካሄዳቸው ጨዋታዎች በመሸነፉ ከፕሪሚየር ሊጉ የመውረድ አደጋ ገጥሞታል።

በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት አሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋን የቀጠረውና በርካታ ተጫዋቾችን ያስፈረመው ዳሽን ቢራ በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሎ ቢጠበቅም ሳይታሰብ እየተንሸራተተ ሂዶ በዓመቱ መጨረሻ ግርጌ ላይ ተገኝቷል። የፕሪሚየር ሊጉ የዋንጫ ባለቤት የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫውን ማንሳቱን ያረጋገጠው ዳሽን ቢራን ሁለት ለአንድ በረታበት እለት ሲሆን ኤሌክትሪክ ደግሞ ከፕሪሚየር ሊጉ አለመውረዱን ያረጋገጠው ከዳሽን ቢራ ጋር እስከ መጨረሻው ሳመንት አንገት ለአንገት ተናንቆ ንግድ ባንክን በማሸነፍ ነው።  

 

 

 


ethiofootball.com
 
 
ዜናውን፣ ጽሑፉን ከወደዱት የፌስቡክ ገጾ ላይ ሼር ያድርጉት
 
 
Your Comment /አስተያየት *   Required
     
Name:
 
Email:
 
 
 
 
Comment:
* Amharic keyboard
   
 
     
     
 
Copyright© 2014 Ethiofootball.com All rights reserved!